የቁርአን ተቃርኖ

ወንጌል ምን ዓይነት መጽሐፍ ነው?

 በJochen Katz

ትርጉምና ቅንብር በአዘጋጁ 

ወንጌልን በተመለከተ ቁርአን የሚከተሉትን ዓረፍተ ነገሮች ይናገራል፡፡

‹በፈለጎቻቸውም (በነቢያቶቹ ፈለግ) ላይ የመርየምን ልጅ ዒሳን ከተውራት በስተፊቱ ያለውን አረጋጋጭ ሲኾን አስከተልን፣ ኢንጂልንም በውስጡ ቀጥታና ብርሃን ያለበት በስተፊቱ ያለችውንም የሚያረጋግጥ ለጥንቁቆችም መሪና ገሣጭ ሲኾን ሰጠነው› 5.46-47፣ ‹ከዚያም በዱካዎቻቸው ላይ መልእክተኞቻችንን አስከታተልን የመርምን ልጅ ዒሳንም አስከተልን ኢንጅልንም ሰጠነው ... ... ›፣ 57.27፡፡ ‹(ሕፃኑም) አለ‹- እኔ የአላህ ባሪያ ነኝ መጽሐፍን ሰጥቶኛል ነቢይንም አድርጎኛል› 19.30፣ ‹ከእርሱ በፊት ያሉትን መጻሕፍት የሚያረጋግጥ ሲኾን መጽሐፉን (ቁርአንን) ባንተ ላይ ከፋፍሎ በውነት አወረደ፡፡ ተውራትንና ኢንጂልንም አውርዷል› 3.3፣ ‹እላንተ የመጽሐፉ ባለቤቶች ሆይ ተውራትንና ኢንጂልን ከጌታችሁም ወደእናንተ የተወረደውን እስከምታቆሙ (እስከምትሰሩባቸው) ድረስ ... › 5.68፣ ‹ለነዚያ ያንን እነሱ ዘንድ በተውራትና በኢንጂል ተጽፎ የሚያገኙትን ... ...› 7.157፣ ‹እርሱ ያ መጽሐፉን የተብራራ ኾኖ ወደ እናንተ ያወረደ ሲኾን ከአላህ ሌላ ዳኛን እፈልጋለሁን? (በላቸው) እነዚያም መጽሐፍን የሰጠናቸው እርሱ ከጌታህ ዘንድ በእውነት የተወረደ መኾኑን ያውቃሉ ከተጠራጣሪዎችም አትኹኑ› 6.114፡፡

እነዚህ ቁጥሮች በሙሉ የሚያሳዩት ወንጌል የክርስትያኖች መጽሐፍ እንደሆነ፣ ከእነሱ ጋር ያለና እንዲሁም የሚያምኑበት መጽሐፍ መሆኑን ነው፡፡ የቁርአን ጸሐፊው እራሱ ያሳሰበው ክርስትያኖች እራሳቸው ያላቸውን ወንጌል (እንዲሁም ቶራን) ሙሉ በሙሉ እንዲያምኑበት ነው፡፡

ቅራኔው

ይሁን እንጂ ችግሩ እዚህ ጋ ነው፣ የክርስትያኖችን መጽሐፍ፣ አዲስ ኪዳንን በምንመለከትበት ጊዜ በየትኛውም ቦታ ላይ ለኢየሱስ የወረደ (ለኢየሱስ የተሰጠ) መጽሐፍ እንደሆነ አይናገርም፡፡ በሌላ መልኩ ግን አዲስ ኪዳን የያዘው በኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮች (ደቀመዛምርቱ) የተጻፉ ብዙ መጽሐፎችን እንደያዘ ነው (ይህም በመንፈስ ቅዱስ ምሪት ስር ጌታ ኢየሱስ ከሞት ተነስቶ ካረገ በኋላ የሆነ ነው)፡፡  

ስለዚህም ኢንጂል ሊሆን የሚችለው፡-  

ሀ. ለኢየሱስ የተሰጠ መጽሐፍ ወይንም ደግሞ

ለ. በክርስቶስ ተከታዮች ተጽፎ ክርስትያኖች እንደ ቅዱስ መጽሐፋቸው የያዙት መጽሐፍ ብቻ ነው፡፡  

ነገር ግን ሁለቱንም ሊሆን አይችልም፡፡ ይሁን እንጂ መሐመድ የገመተው ነገር፣ የክርስትያኖችና የአይሁዶች ቅዱስ መጽሐፍ ከቁርአን ጋር በጣም ተመሳሳይ ይሆናል በማለት ነበር፣ ይህም እርሱ ከአላህ ተቀበያለሁ በማለት እንዳሰበው መጽሐፍ ነው፡፡ ይሁን እንጂ መሐመድ ስለ ሁኔታው (ማለትም ስለመጽሐፍ ቅዱስ አጻጻፍ) ምንም የሚያውቀው ነገር አልነበረውም፡፡ የቁርአንና የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ባህርያት ሙሉ በሙሉ የተለያዩ ናቸው፡፡ መሐመድ ቁርአንን በተቀበለበት በተመሳሳይ መንገድ ለኢየሱስ ተሰጠ የሚለው መጽሐፍ የለም፣ ክርስትያኖችም እንደዚህ ዓይነት መጽሐፍ ስለመኖሩ በየትኛውም ዘመንና ጊዜ በፍፁም ተናግረው አያውቁም፡፡ ከዚህ በላይ ያየነው የቁርአን 5.46 አባባል ከመሐመድ አዕምሮ ውስጥ የመነጨ የተሳሳተ ሐሳብ ነው፡፡

የቁርአን ጸሐፊው በ5.46 እና በ19.30 ላይ እንዳሉት ዓረፍተ ነገሮች ብቻ አስቀምጦ ቢሆን ኖሮ ሙስሊሞች እንደሚከተለው ለማለት ጥሩ አማራጭን ይሰጣቸው ነበር፣ ማለትም ‹ለኢየሱስ የወረደው መጽሐፍ ጠፍቷል› ብለው ለማለት ይመቻቸው ነበር፡፡ እንዲሁም ደግሞ በቁርአን ትርጉም መሠረት አዲስ ኪዳን ከኢንጂል ሙሉ ለሙሉ የተለየ ነው በማለት ሙስሊሞች ሊናገሩና፣ ስለዚህም በክርስትያኖች አዲስ ኪዳን አናምንም ቁርአን አይቀበለውም (አይደግፈውምና) በማለት ሊደመድሙ ይችሉ ነበር፡፡

ይሁን እንጂ ከዚህ በላይ ያለው ሁለተኛው ዓይነት አረፍተ ነገር እንደዚህ ዓይነት ዓረፍተ ነገሮችን እንዳናደርግ ይከለክለናል፡፡ ምክንያቱም ቁርአን ኢንጅልን የክርስትያኖች መጽሐፍ እንደሆነ ይገልጠዋልና ነው፡፡ ስለሆነም ኢንጅል የክርስትያኖች መጽሐፍ ስለሆነ ቁርአን ስለ ኢንጅል ባህርያት እጅግ በጣም ጭፍን የሆነ ስህተትን ተናግሯል፡፡ እሱም (ወንጌል) ለኢየሱስ የተሰጠም የኢየሱስም መጽሐፍ አይደለም፡፡ (ከላይ እንዳየነው በመንፈስ ቅዱስ መሪነት በጌታ ኢየሱስ ደቀመዛምርት የተጻፈ ነው እንጂ)፡፡

የቁርአን ሐሳብ ምንጩስ?

እንደዚህ ዓይነት ስህተት በመሐመድ አዕምሮ ውስጥ እንዴት ሊነሳ ቻለ? መሐመድ በማርቆስ ወንጌል የመጀመሪያው ቁጥር ላይ ያለውን ዓይነት አረፍተ ነገር ‹የእግዚአብሔር ልጅ የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል መጀመሪያ›  ስምቶ ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህም በስህተት ያሰበው ይሄ አነጋገር ልክ እንደ ሙሴ ሕግ ነው ዓይነት መሆን አለበት በማለት ነው፡፡ ማለትም ለአንድ ነቢይ የተሰጠው ትንቢት በመጽሐፍ መልክ ነው በማለት ነው፡፡ ይሁን እንጂ የማርቆስ ወንጌል ዓውዱ እንደሚያሳየው ከሆነ ‹ይህ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ጅማሬ› የሚናገር ነው፡፡ ወንጌልም ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወትና ትምህርት የሚነግረን መልእክት ነው፣ እሱም የተጻፈው በክርስቶስ ተከታዮች ነው እንጂ ለኢየሱስ ለራሱ የተሰጠ መጽሐፍ አይደለም፡፡

መሐመድ የራሱን ልምምድ ማለትም (እንደወረደለት የተናገረውን) የመጽሐፍን መገለጥ (ቁርአንን) ለኢየሱስም ሲያደርገው ነው የምንመለከተው፡፡ ይህም በኢየሱስ ተከታዮች ዘንድ ቅዱስ ተብሎ የተያዘው መጽሐፍ ለኢየሱስ የተሰጠ መጽሐፍ መሆን አለበት በሚል ቀላል ግምት ነው (ይህምለመሐመድ ተሰጠው እንደተባለው እንደ ሙስሊሞች ቁርአን መሆኑ ነው)፡፡ ይሁን እንጂ መሐመድ ስለዚህ ነገር ፍፁም ተሳስቶ ነበር፣ ይህም ስህተት ቁርአንን የስህተት መጽሐፍ አድርጎ ያጋልጠዋል፡፡ ቁርአን የመለኮት መገለጥ መጽሐፍ አይደለም ነገር ግን የተሳሳቱት የጸሐፊው እጅግ ብዙ ግምቶች ጥርቅም ነው እንጂ፡፡

ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ ተለውጧል

በብዙ ሁኔታዎች ላይ ቁርአን መጽሐፍ ቅዱስን ሲቃረን፣ ሙስሊሞች የሚጮኹት ‹መጽሐፍ ቅዱስ ግን ተለውጧል› በማለት ነው፣ ይህንንም የሚያደርጉት እንደዚህ ዓይነቱ መልስ ለሁሉም ችግር ብቸኛ መፍትሄ አንደሆነ በመቁጠር ነው፡፡

ነገር ግን እንደዚህ ዓይነት መልስ ለችግሩ መልስ የማይሰጥበት ሁለት ምክንያቶች አሉ እነሱም፡-  

አንደኛ፡- ኢንጅል ተሳስቷል በማለት ቁርአን በፍፁም ተናግሮ አያውቅም፡፡ በእርግጥ በአይሁዶች ላይ የተወሰኑ ውንጀላዎች አሉ፣ ነገር ግን ክርስትያኖች መጽሐፋቸውን እንደለወጡት የሚናገር ምንም ውንጀላ በቁርአን ውስጥ የለም፡፡ ቁርአን ስለመጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል የሚለው ጽሑፍ ይህንን ጉዳይ በቅርብ ይገልጠዋል እናም ሙስሊሞች መጽሐፍ ቅዱስ ተለውጧል በማለት የሚሉትን ነገር ቁርአን እንደማይደግፈው በግልጥ ያሳያል፡፡

ሁለተኛ፡- የአንዳንድ አንቀፆች መለወጥ ቢኖርም፣ የጥቃቅን (የፊደላት ወይንም የቁጥር ለውጦች መኖር) በጣም ትንሽ የሆነ የትርጉም ለውጥ ያስከተሉ ቢኖሩም እንኳን፣ (እንደዚህ ዓይነት ለውጦች በእጅ ቅጂ ወቅት ሊኖር የሚችል በመሆኑ)፣ ይህ ከዚህ በላይ ያለውን የቁርአንን ተቃርኖ ሊያብራራ በፍፁም አይችልም፡፡ እዚህ ላይ እኛ የምንመለከተው በመጽሐፎቹ ተፈጥሮ ላይ (በቁርአንና በመጽሐፍ ቅዱሰ ላይ) መሠረታዊ ልዩነቶች መኖራቸውን ነው፣ ይህም ልዩነት ለአዝጋሚ ወይንም ለድንገተኛ ለውጥ ሊወሰድ የሚችል ነው፡፡

ለማብራራትም፡- ቁርአን (እንደሚባለው) ከአላህ ዘንድ ለመሐመድ የተላከ መጽሐፍ ነው፡፡ እሱም በመሐመድ እንዳልተጻፈ ይገመታል ነገር ግን በአላህ ለእርሱ ተሰጠ፡፡ በሌላ ጎኑ ደግሞ ሐዲት የመሐመድ ተከታዮችና ጓዶቹ ስለ መሐመድ የተጸፉ ትዝታዎች ናቸው፣ እነዚህም የተመሰረቱትና የተጻፉት በሙስሊሞች ነው ይህም መሐመድ ከሞተ በኋላ እጅግ በጣም ቆይቶ ነው፡፡ እነሱም መሐመድ የተናገራቸውና ያደረጋቸው ነገሮች ስብስቦች ናቸው፡፡ ታዲያ ቁርአንን (ለመሐመድ የተሰጠውን መጽሐፍ) ለመለወጥ ለአንድ ሰው የሚቻል ነገር ነውን? የሙስሊሞች ማህበረሰብ የቅዱስ መጽሐፋቸውን ማለትም ቁርአናቸውን ከእነሱ እውቀት ውጪ ወደ የሐዲት ስብስቦች ማለትም ወደ አንድ ሙሉ ለሙሉ የተለየ ነገር ለመለወጥ ይቻላልን?

ለዚህ ጥያቄ የሙስሊሞች መልስ የሚሆነው ያለምንም ጥርጥር ትልቅ አይሆንም ነው፡፡ ነገር ግን ይሄ ለሙስሊሞች መጽሐፍ የማይቻል ከሆነ፣ ታዲያ ለምንድነው ሙስሊሞች እንዲህ ዓይነት ነገር በክርስትያኖች ማህበረሰብ ውስጥ ሆኗል በማለት ሊያስቡ የሚችሉት? በመጀመሪያ ክርስትያኖች ‹ለኢየሱስ የተሰጠ መጽሐፍ አላቸው› ነገር ግን አንድ ቀን ሲነቁ ቅዱስ መጽሐፋቸው የኢየሱስ ተከታዮች የጻፏቸው ስብስቦች ሆነው ማናቸውም ሳያውቁ ተለወጡባቸው ስለዚህም ማንም ሰው አላወቀም ማንም ሰውም ምንም ዓይነት ተቃውሞንም አላቀረበም ማለት ነው? እንደዚህ ዓይነት ፅነሰ ሐሳብን ተቀብሎ ማመን የሚጠይቀው ነገር እጅግ በጣም እውር የሆነ እምነትን ነው፡፡ ይህ ደግሞ በፍፁም የማይሆን ነው፡፡ ትንሽ ማለትም ዝቅተኛም በሆነ የማስተዋል አመለካከት እንኳን ሲታሰብ ይህ ይሆናል ብሎ ማንም ሰው ሊደመድም አይችልም፡፡ እናም ይህ የሚያመለክተው የቁርአን ጸሐፊው የክርስትያኖችን መጽሐፍ በተመለከተ በቀላሉ የፈፀመው ነገር ስህተት መሆኑን ብቻ ነው፡፡

የአዘጋጁ ማሳሰቢያ

ከላይ የቀረበው አጭር ጽሑፍ በክርስትያኖች ቅዱስ መጽሐፍና በሙስሊሞች ቁርአን መካከል ትልቅ ልዩነትን መኖሩን ያሳያል፡፡ እንደሚታወቀው ሁለቱም የሃይማኖት ተከታዮች መጽሐፍት ናቸው፡፡ ሁለቱም እናምናለን የሚሉት አንድ አምላክን ነው፡፡ በመሆኑም በሁለቱ መካከል ያለው ልዩነት በአንድ ጊዜ ቢሆን ሁለቱም ትክክል ናቸው ማለት እንደማይቻል ያሳያል፡፡ ትክክል የሚሆነው ከሁለቱ አንዱ ብቻ ነው፡፡ ከዚህች አጭር ጽሑፍ እንደምንረዳው ከሆነ የቁርአኑ ጸሐፊ በጣም ትልቅ ስህተትን እንደፈፀመ ነው፡፡ ይህም እውነታ ቁርአንን እንደ አንድ የሃይማኖት መጽሐፍ የዘላለም ሕይወታችንን ጉዳይ በተመለከተ እምነት እንዳንጥልበት እና ውድቅ እንድናደርገው የሚያሳስብ ነው፡፡

ይሁን እንጂ አንድን ትክክል ያልሆነ ነገር ውድቅ ማድረግ ብቻውን ለሕይወት መፍትሄ ሊሆን አይችልም በመሆኑም በስህተት ምትክ የምንታመንበት እውነትና ትክክለኛ እምነት ላይ መምጣት አለብን፡፡

የዚህ ገፅ አዘጋጆች ለሙስሊም አንባቢዎች በፍቅርና በትህትና መጽሐፍ ቅዱስን አግኝተው እንዲነቡ የሚያሳስቡት ለዚህ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ወጥ መልእክት አለው እሱም የዘላለም ሕይወት የሚገኝበትን ተስፋ ቃል መግለጥ ብቻ ነው፡፡ የዘላለም ሕይወትን ለኃጢአተኛው ሰው ለመስጠት እግዚአብሔር የከፈለውን ክቡር ዋጋ ለእውነት ፈላጊዎች የሚገልጥ ነው፡፡ ስለዚህም ጊዜ እና ትኩረትን ሰጥታችሁ እንድታነቡት እና በእግዚአብሔርም ፊት ቀርባችሁ እራሱ በገባው የዘላለም ሕይወት ስጦታ ቃል ኪዳን መሰረት በጌታ በኢየሱስ በኩል የኃጢአት ይቅርታ እንዲሰጣችሁ ጠይቁት፡፡ እራሱ ኃጢተኞች ከራሱ ጋር እንዲታረቁ በሰራው ስራ ይቀበላችኋል አዲስንም ሕይወት ይሰጣችኋል እርሱ በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን በኩል ለሚመጡት ይቅር የሚል ነውና፡፡ ጌታ ኢየሱስ እራሱ በፀጋው ይርዳችሁ አሜን፡፡  


የትርጉም ምንጭ: Quran Contradiction  What kind of book is the Injil?  Jochen Katz

ለእስልምና መልስ አማርኛ  ዋናው ገጽ