የቁርአን የመጀመሪያ ምንጮች
በREV. W. ST. CLAIR TISDALL, M.A., D.D
ትርጉምና ቅንብር በአዘጋጁ
ምዕራፍ ሦስት ክፍል አንድ
የሳቢያንና የአይሁዶች ሐሳቦችና ልማዶች ተፅዕኖዎች
አረቦቹ የሚስማሙባቸው ብዙ የሃይማኖት ሐሳቦችና ልምምድ ቢኖራቸውም፣ መሐመድ እንደ ነቢይ በተገለጠበት ጊዜ ግን መለኮታዊ መገለጥ ያለበት የሚመስል ምንም ጥራዝ አልነበራቸውም፡፡ በመሆኑም መሐመድ ወደ አባቶቻቸው ንፁህ እምነት እንዲመልሳቸው ለመምራት የተሾመ እንደሆነ ሊናገር የሚያስመስለው ምንም ነገር አልነበራቸውም፡፡ ነገር ግን በአረቢያ ውስጥ ይኖሩ የነበሩ አንዳንድ ማህበረ ሰቦች ከእግዚአብሔር የመጣ መጽሐፍ እንዳላቸው ይናገሩ ነበር፡፡ መሐመድና ተከታዮቹም ለእነዚህ የሃይማኖት ቡድኖች ምንም ትኩረትንና ክብርን አልሰጡም፡፡ ‹የመጽሐፉ ሰዎች› የሚለው ርዕስ በተለይም ተሰጥቶ የነበረው ለአይሁዶችና ለክርስትያኖችም ጭምር ነበር፡፡ ለዚህም ግልጥ የሆነ ማስረጃ በቁርአን ውስጥ ይገኛል፡፡ በአረቢያ ውስጥ የነበሩት መጽሐፍ ያላቸው አራቱ ሃይማኖቶችም አይሁዶች፣ ክርስትያኖች እና ማግያን ወይንም ዞሮአስተሪያንስ እና ሳባውያን ነበሩ፡፡ እነዚህም ሁሉም በአንድ ላይ በቁርአን 22 ቁጥር 17 ላይ ተጠቅሰዋል፡፡ ‹እነዚያ ያመኑ እነዚያም ይሁዳውያን የኾኑ ሳቢያኖችም ክርስትያኖችም መጁሶችም እነዚያም (ጣዖታትን በአላህ) ያጋሩ አላህ በትንሣኤ ቀን በመካከላቸው በፍርድ ይለያል አላህ በነገሩ ሁሉ ላይ በእርግጥ አዋቂ ነውና›፡፡ እነዚህም እያንዳንዳቸው በማደግ ላይ ባለው እስልምና ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖዎችን እንዳሳደሩ እንመለከታለን፡፡ ነገር ግን ሳቢያንን በተመለከተ ያለው ነገር በምንም መንገድ ጥቂት ሊሆን አይችልም፡፡ ስለዚህም እኛ የምንጀምረው ስለ እነዚህ ቡድኖች የሚታወቀውን ነገር በመጥቀስ ነው፣ እነሱም በቁርአን 2.59 ላይ ‹እነዚያም የበደሉት ሰዎች ከዚያ ለነሱ ከተባሉት ሌላ ቃልን ለወጡ በነዚያም በበደሉት ላይ ያምመጡ በመኾናቸው ምክንያት መቅሰፍትን አወረድንባቸው› ተብለውም ተጠቅሰዋል፡፡
ስለ ሳቢያን ያለን እውቀታችን መጠነኛ ነው ነገር ግን ለዓላማችን ብቁ ነው፡፡ በአቡ ፊዳ የተጠቀሰው ቀደምቱ የአረብ ጸሐፊ አቡ ኢሳል ማግሀሪቢ ስለ እነሱ የሚከተለውን ዘገባ ሰጥቷል፡፡ ‹ሶርያውያኖች ከሁሉ የቀደሙ ሕዝቦች ናቸው (አገሮች) አዳምና ልጆቹ የእነሱን ቋንቋ ተናግረዋል፡፡ የእነሱም የሃይማኖት ማህበረሰቦች ሳባውያን ነበሩ እነሱም ሃይማኖታቸውን ያገኙት ከሴትና ከኢድሪስ (ሄኖክ) እንደሆነ ያዛምዳሉ፡፡ እነሱም ‹የሴት መጽሐፍ› በማለት የሚጠሩት መጽሐፍ አላቸው ይህም ከሴት የመጣ ነው በማለት የሚጠሩት ነው፡፡ በውስጡም ጥሩ የሆኑ የስነ ምግባር መሰረቶች ተመዝግበውበታል፣ ለምሳሌም እውነትን የመናገር ምክር ማበረታታንንና ለእንግዳ ጥበቃ ማድረግን፣ እንዲሁም ክፉ የሆኑ ልማዶች ተጠቅሰው ከእነሱ ስለመቆጠብም ምክር አለበት፡፡› ሳባውያን የተወሰነ ዓይነት የሃይማኖት ልምምድ አላቸው ከእነሱም መካከል ሰባት የሆኑ ውሱን የፀሎት ሰዓቶች አሉባቸው፡፡ አምስቱም ሙስሊሞች አሁን ካሏቸው ጋር ይመሳሰላሉ፡፡ ስድስተኛው ፀሐይ ስትወጣ የሚሆንና ሰባተኛው ደግሞ ሌሊት ስድስት ሰዓት ከመሆኑ በፊት የሚደረግ ነው፡፡ ፀሎታቸው ልክ እንደ ሙስሊሞቹ ነው፣ ማለትም እውነተኛ የሆነ ትጋትን የሚጠይቅ ነበር፡፡ አምላኪውም ይህንን በሚያደርግበት ጊዜ ሐሳቡን እንዲበታተን ክፍተት መስጠት አልነበረበትም፡፡ በሞተ ላይ ይፀልዩ ነበር ነገር ግን በማጎንበስ ወይንም ወደ መሬት በመደፋት አልነበረም፡፡ እንዲሁም ለሰላሳ ቀናት ይፆሙ የነበረ ሲሆን የጨረቃው መውጣት ወር አጭር ከሆነ ደግሞ ፆሙን ለሃያ ዘጠኝ ቀናት ያደርጉት ነበር፡፡ ከፆማቸውም ጋር አያይዘው የፈጢርንም በዓል ያከብሩ ነበር (በወሩ መጨረሻ ላይ የሚደረግ የፆም መግደፍ)፡፡ እንዲሁም ደግሞ ሂላል (አዲስ ጨረቃን)፡፡ በዚህ መንገድ የፈጢር በዓል ይሆን የነበረው ፀሐይ በአይሪስ (በሰሜን ባለው የከዋክብት ክምችት) ውስጥ ስትገባ ነው፡፡ እነሱም ይፆሙ የነበረው ከአራተኛው ሌሊት (ማለትም ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት) ጀምሮ የፀሐይ ክብ እስክትጠልቅ ድረስ ነበር፡፡ እንዲሁም ደግሞ በአምስቱ ፕላኔቶች ወደ ክብራቸው ቤት (አዳራሽ) መውረድ ጊዜ ትልቅ ክብረ በዓልን ያደርጉ ነበር፡፡ እነዚህም አምስቱ ፕላኔቶች ሳተርን፣ ጁፒተር ማርስ ቬኑስ እና ሜርኩሪ ናቸው፡፡ እንዲሁም ደግሞ የመካን ቤት ማለትም ካኣባን ያከብሩ ነበር፡፡
ከዚህ ዘገባ በግልፅ የምናስተውለው፣ ሙስሊሞች በሃይማኖት ልምዳቸው የሚያደርጓቸውን በጣም ብዙዎቹን ነገሮች የተዋሷቸው ከዚህ ድብቅ ከሆነው ሃይማኖት ውስጥ ነበር፡፡ እነሱ ግን የሚያምኑት መሐመድ በመልአኩ ገብርኤል በኩል ከእግዚአብሔር ያመጣቸው ናቸው በማለት ነው፡፡ ለምሳሌ የሙስሊሞች የረመዳን ፆም ለአንድ ወር ነው፣ የሚደረገውም ከጠዋት እስከ ማታ ነው፣ ሆኖም የአንድ ቀን ትክክለኛው መጀመሪያና የአንድ ቀን ትክክለኛው መጨረሻ ሕግ የተወሰደው ከአይሁዶች ነው፡፡ በዚህም መሠረት በቅዱሱ የፆም ወራት ውስጥ የእያንዳንዱን ቀን መጀመርና መጨረስ ለማስታወቅ በፐርሺያውያን ዘንድ እንዲሁም በሌሎች አንዳንድ አገሮች መድፍ ይተኮሳል፡፡ በፆም ወርም መጨረሻ ላይ የፈጢር በዓል በመሐመዳውያን ዘንድ ይከበራል፡፡ እንዲሁም ሙስሊሞች በጣም የታወቀው በየቀኑ አምስት የመፀለያ ጊዜ ቢኖራቸውም እንደ አስፈላጊነቱ የሚደረጉ ሁለት ተጨማሪ የፀሎት ሰዓታትም ይገኛሉ፡፡ ይህም ልክ ሳባውያን እንዳላቸው ሰባት የፀሎት ቁጥር ነው፡፡ ማጎንበስ (ራኩ) እና ተደፍቶ መስገድ (ሱጁድ) በመሐመዳውያን አምልኮ ቢበረታታም በሞተ ሰው በሚደረግ ፀሎት ላይ ግን አይደለም፡፡ በመጨረሻም የምናየው ሙስሊሞች አሁንም ካኣባን በጣም እንደሚያከብሩት ነው፡፡ በእርግጥ እነዚህ ሁሉ ልምምዶች በቆይራሽ ጎሳዎችና በሳባውያን መካከል በጣም የተለመዱ ነበሩ፡፡ መሐመድ ብዙዎቹን የሃይማኖት ልምምዶች ከሳባውያን እና በአጠቃላይም ከሃይማኖታቸው ወስዷል የሚለው አባባል (ምናልባትም ከእሱ ጥንታዊ ነው የሚል አባባል ጋር) በእስልምና አመሰራረት ላይ ትልቅ ተፅዕኖን አድርጓል፣ ይህም እውነታ የተረጋገጠው የጣይፍና የመካው ባኑ ጃዲማህ ለካሊድ ወደ መሐመዳውያንነት መለወጣቸውን ባወጁበት (በገለጡበት) ጊዜ ነበር እነርሱም ያንን ያደረጉት እንደሚከተለው በመጮኽ ነበር ‹እኛ ሳባውያን ሆነናል!!› በማለት ነበር፡፡
ሳባውያን ‹ከፊል ክርስትያን› ሃይማኖታዊ ቡድን ተብለው ይታሰቡ ነበር፡፡ ሌሎች ደግሞ የፈረጇቸው ከማንዲያንስ ጋር ነበር፣ የማንዲያንስ ሃይማኖት የኖስቲሲዝም እና የጥንታዊ ባቢሎናውያን አምልኮ እንግዳ የሆነ ውጥንቅጥ ነው፡፡ ምንም እንኳን በመርሆው ፀረ ክርስትያን ቢሆንም ከማጊዝም፣ ከአይሁዲዝም እና ከክርስትናም አንዳንድ ነገሮችን መበደሩ እውነት ነው፡፡ ማንዲያኖች ስማቸውን ያገኙት ከማንዳ ነው፣ ይህም እነሱ የሚያምኑበት በጣም ጠቃሚውና ወይንም ዘላለማዊው ግልጠት ነው፡፡ በእነርሱም ቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ እርሱ የተጠራው ‹ሲድራ ራባ› ተብሎ ሲሆን እራሱንም በተከታታይ በተለያየ ጊዜ ሰው አድርጎ እንደገለፀ ነው፡፡ ከእነርሱም ውስጥ የመጀመሪያዎቹ ሦስቱ፡ አቤል፣ ሴት እና ሄኖክን ሆኖ እንደተገለጠና፣ እንዲሁም በመጨረሻው ደግሞ መጥምቁ ዮሐንስ ሆኖ ነው፡፡ መጥምቁ ዮሐንስም በመሲሁ በኢየሱስ ላይ ጥምቀትን አካሂዷል፣ ኢየሱስም በመጨረሻ ወደ ብርሃን መንግስት ተመልሷል፣ ይህም ስቅለትን የተሰቀለ ከመሰለ በኋላ ነው፡፡ ይህ የሁለተኛውና ጌታ ኢየሱስን በተመለከተ የሰፈረው ሐሳብ በቁራን ውስጥ ተደግሟል (ቁርአን 4.159) ኋላም ቆይቶ ትኩረት ይሰጥበታል፡፡
ስለ ሳባውያን ያለን ውሱን የሆነ እውቀትና ማንዲያንስ ከእነርሱ ጋር አንድ ዓይነት ናቸውን የሚለው ጥርጥር፣ ሳባውያን በእስልምና ላይ ያስከተሉትን ሰፊና ጠቃሚ ተፅዕኖ ሙሉ ለሙሉ ለማየት የማይቻል አድርጎታል፡፡ መሐመድ እጅግ በጣም ብዙ ወደተዋሳቸውና፣ የእርሱ ሃይማኖት፣ የኋለኛዎቹን የአይሁድ እምነት ‹የኑፋቄ እምነት ብሎ ወደጠራው› ወደ አይሁዶች እንመለሳለን፡፡ በመሐመድ ጊዜ የነበሩት አይሁዶች ብዙ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን በአረቢያ የተለያዩ ቦታዎች ላይ እጅግ በጣም ኃይለኞችም ነበሩ፡፡ በዚያም አገር ብዙዎቹ በተለያየ ጊዜ መስፈራቸው ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ይህም የተለያዩ ጦረኞችን ማለትም ፓለስታይንን ያስገበሩና ያፈራረሱትን፤ ለምሳሌም - ናቡከደነፆርን፣ የታላቁ አሌክሳንደር ተኪዎችን፣ ፖምፔይን፣ ቲቶን ሃድሪያንን እና ሌሎችንም በመሸሽ ነበር፡፡ በተለይም አይሁዶች በመዲና አጎራባቾች ውስጥ እጅግ በጣም ብዙ ነበሩ፣ በአንድ ወቅትም መዲናን በሰይፍ ይዘዋት ነበር፡፡ በመሐመድ ጊዜ ሦስቱ የአይሁድ ታላላቅ ጎሳዎች ባኑ ቁራዲሃህ፣ ባኑ ናድር እና ባኑ ቃይኑቃ ነበሩ፡፡ በመዲና አጎራባቾች ላይ ሰፍረውና በጣምም ኃይለኞች ስለነበሩ መሐመድ በ622 መዲና እንደገባ ከእነርሱ ጋር የማጥቃትና የመከላከል ስምምነቶችን አድርጓል፡፡ ሌሎችም የአይሁድ አጎራባች ሰፋሪዎች በካይባር እና በዋዲ ዑልቃራ እንዲሁም በአካባህ ባህረሰላጤ ጠረፎች ላይ ነበሩ፡፡ አይሁዶች በመገለጥ የመጣ መጽሐፍ ያላቸው መሆኑ እንዲሁም የአብርሃም ዘር መሆናቸው፣ ይህንንም ቁራይሾችና ሌሎችም ጎሳዎች እንደነሱ እንደሆኑ አድርገው የሚናገሩለት ስለነበር ለእስራኤላውያን ትልቅ ክብርና ተፅዕኖንም ሰጥቷቸው ነበር፡፡ ስለዚህም የአገር በቀል አፈታሪኮች ከአይሁድ ታሪክና ባህላዊ ልማድ ጋር የመዋሃድን ሂደት አካሂደው ነበር፡፡ ጠቅለል ባለ መንገድ የፓለስቲናውያን ታሪክ የሂጃዞች ታሪክ ሆኖ ነበር፡፡ የካአባ ቅጥር ግቢ ቅዱስ ይደረግ የነበረው ‹የአጋር የጣር ስፍራ› ተብሎ ነበር፡፡ እንዲሁም ደግሞ የዘምዘም ቅዱስ የውሃ ጉድጓድ የእርሷ ጭንቀት እረፍት ምንጭ እንደነበረ ተደርጓል፡፡ ወደ መካ የሚጓዙት ሰዎች በሳፋና በማርዋ መካከል በፍጥነት የሚመላለሱት የእርሷን ውሃ የመፈለግን ችኮላ ለማስታዎስ ነበር፡፡ ቤተመቅዱስንም የገነቡት አብርሃምና እስማኤል ነበሩ፣ በግድግዳውም ውስጥ ጥቁሩን ድንጋይ የተከሉት እነርሱ ናቸው፣ ወደ አራፋት የሚደረገውንም ሐጂ ለአረቢያ ሁሉ ያደረጉት እነርሱ ናቸው፡፡ እርሱንም የሰይጣን ምስል በማስመሰል ሐጂ አድራጊዎቹ ድንጋይን በእርሱ ላይ ይወረውሩ ነበር፣ እንዲሁም በሚና የሚደረገው መስዋዕትም አብርሃም ላደረገው የተለያዩ ዓይነት መስዋዕቶች ማስታዎሻ ይሆን ዘንድ ነበር፡፡ የአገሩ የሃይማኖት ስርዓት ምንም ጥቂት የነበረ ቢሆንም በእስራኤላውያን አፈ ታሪክ ውርስ ተተክቶ ነበር፡፡ እነርሱም ሙሉ በሙሉ አዲስ በሆነ ሌላ ብርሃን ተቀባይነትን አግኝተው ነበር፣ እንዲሁም የእግዚአብሔርን ጓደኛ አብርሃምን በአረብ አስተሳሰብ የቀደሰና ያከበረ ከመሰለ ነገር ጋር ግንኙነትን በማድረግ ነበር፡፡ በዚህ የጋራ አቋም ላይ መሐመድ የራሱን እርምጃ ወሰደና ለሕዝቡ አዲስና መንፈሳዊ ስርዓትን አወጀ፣ ይህንንም ያደረገው የአረቢያ ባህረ ሰላጤ በሙሉ ለዚህ ጥሪ ምላሽን እንዲሰጥ በሚናገር ድምፀት ነበር፡፡
የካኣባ ስርዓት እንዳለ ተጠብቆ ቢሆንም ከጣዖታት ዝንባሌዎቹ ሁሉ ተገፎ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ እንግዳ የሆኑ ትርጉም ያልተሰጣቸው (የሌላቸው) ሽፋኖች፣ በእስላም አምላካዊ እምነት ውስጥ አሁንም አላቸው፡፡ ከአብርሃም ዘሮች ጋር መተዋወቁ የነፍስን ዘላለማዊነትና የሙታን ትንሳኤ መኖርንም አስተምህሮ እንዲታወቅ አድርጓል፣ ነገር ግን እነዚህም ከብዙዎች የአረቢያንስ ግሩም ሐሳቦች ጋር በአረቢያንስ እድገት ውስጥ ነበሩ፡፡ ብቀላ ተስሎ የነበረው የተገደለው ሰው ነፍስ በገዳዩ ላይ እንደ ወፍ ለብቀላ ጭው ጭው እያለች ስትጮኽ፣ እንዲሁም ግመል በባለቤቱ መቃብር አጠገብ ለረሃብ ሲጣል ነበር፣ ያም እርሱ በትንሳኤ እርሱን ለመሸከም ዝግጁ እንዲሆን ነበር፡፡ እጅግ በጣም ብዙ የሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ቋንቋዎችም በጋራ ጥቅም ላይም ውለው ነበር፣ ወይንም ደግሞ ቢያንስ በብቃት በጋራ አግልግሎት ላይ ውለው ነበር፡፡ እምነት፣ ንስሐ፣ መንግስተ ሰማይና ሲዖል፣ ሰይጣን እና መላእክቱ፣ የሰማያት መላእክት፣ ገብርኤል የእግዚአብሔር መልእክተኛ ሁሉ ከአይሁዳዊ ምንጭ የተወሰዱ ነገሮች ናቸው፡፡ እነርሱም በወቅቱ እዚያው የነበሩ ወይንም ደግሞ ለመወሰድ የተዘጋጁ ነበሩ፡፡ በተመሳሳይም መንገድ የሰው ውድቀት ታሪክ፣ የዘፍጥረት፣ የጥፋት ውሃ፣ የከተማዎችና የአገሮች ውድመት እና ወ.ዘ.ተ፡፡ ስለዚህም በመሐመድ እጅ ውስጥ ዝግጁ የሆኑና ዙሪያውን የከበቡት እጅግ በጣም ሰፊ የሆኑ ብዙ ሐሳቦች የታጨቁበት መሰረታዊ ነገሮች ነበሩ፡፡
የቀደሙት የአረብ ጸሐፊዎች የጠቆሙን ነገር መሐመድ በተነሳበት ጊዜ አይሁዶች መሲህ እንደሚመጣ እየጠበቁ እንደነበርና የሚመጣው ነቢያቸው በጠላቶቻቸው ላይ የሚወስደውን ብቀላ በማንሳት ጠላቶቻቸውን ማስፈራራት ልማዳቸው እንደነበር ነው፡፡ ይህም ከአረቦች መካከል አንዳንዶቹ መሐመድ እንደሚመጣና ትንቢት እንደተነገለትናነቢይ እንዲቀበሉት እንደመራቸው ምንም ጥርጥር የለውም፣ በተለይም የመዲናዎቹን ባኑ ካዛርጃ (ኢብን ኢሻክ እንዳለው)፡፡
መሐመድ ያወጀው ነገር እርሱ በመለኮት የተሾመው አዲስ ሃይማኖትን እንዲመሰርት ሳይሆን ሰዎችን ወደ ‹አብርሃም እምነት› እንዲጠራ እንደሆነ ነበር፡፡ ስለዚህም አይሁዶችን በእርሱ ጎን እንዲቆሙ መታገል ወይንም መጣጣር ለእርሱ የተለመደ ነገር ነበር፡፡ ይህንንም በመዲና ለማድረግ ጥሯል፡፡ ለተወሰነም ጊዜ መጠነኛ መሳካትንም ያገኘ መስሎ ነበር፡፡ በዚህም ጊዜ የወሰደው አንድ እርምጃ የዚህን ዓላማ በጣም በግልጥ አሳይቶ ነበር፡፡ እርሱም ኢየሩሳሌምን የእምነቱ መስገጃ አቅጣጫ ማድረጉና ተከታዮቹም በሚፀልዩበት ጊዜ ፊታቸውን ወደ ኢየሩሳሌም እንዲያዞሩና በዚህም አይሁዶችን እንዲመስሉ መርቷቸው ነበር፡፡ ቆይቶ ከአይሁድ ጋር ሲቃቃርና ከአረቦች ጋር መቀራረብን በጣም ጠቃሚ ሆኖ ሲያገኘው መካን የመፀለያ አቅጣጫ አድርጎ ቀየረው፣ ይህም ደግሞ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በሙስሊሞች መካከል ቀጥሏል፡፡ መዲና እንደደረሰ ደግሞ አይሁዶች የመንፃትን ቀን ሲያከብሩ አይቶ፣ ወዲያውኑ ተከታዮቹም እንደዚያ እንዲያከብሩ አዘዛቸው፡፡ እንዲያውም የቀኑንም ስም በአይሁዶች ዘንድ የሚታወቅበትን ስያሜ በመውሰድ (በአረብኛ አሹራ) በማለት ጠርቶታል፡፡ በዚህ ወቅት የሚደረገውም መስዋዕት የአሕዛብ አረቦች ወደ መካ ሐጂ ጉዞ በሚያደርጉበት ጊዜ በሚና ሸለቆ ውስጥ ከሚያደርጉት የበለጠ እንዲሆን ታቅዶ እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ስለዚህም አብርሃም እስማኤልን የሰዋበት ነው በማለት ሙስሊሞች የሚያከብሩትን ክብረ በዓል (ሙስሊሞች እንደሚሉት) ኢድ አል ዱሃን መሐመድ የመሰረተው ሚያዝያ 624 ዓ.ም ከአይሁዶች ከተጣላ በኋላ ነበር፡፡ በዚህም እንኳን የምናየው የአይሁድ እምነት በእስልምና ላይ ያስከተለውን ተፅዕኖ ነው፡፡ ይህም በዓል አሁንም በሙስሊሞች ይከበራል፡፡ መሐመድ የአይሁድን ልምምድ የጀመረው በኢድ ቀን ሁለት መስዋዕቶችን በማቅረብ ነበር፡፡ ይህም ሁለት ሕፃናትን በማረድ ነው አንዱን ለሕዝቡ ሁለተኛውን ደግሞ ለእራሱ በማቅረብ ነው፣ ይህም የአይሁድን የመንፃትን ቀን ስርዓት በማዘዋወር ነበር ማለትም አንድ የአይሁድ ካህን በመጀመሪያ ለእራሱ ቀጥሎም ለአገሩ ሕዝብ በአጠቃላይ መስዋዕትን የሚያቀርበውን በማለዋወጥ ነው፡፡ በእነዚህ ነገሮች የምናስተውለው የአይሁዳውያን ስርዓት ተፅዕኖ በመሐመድ ላይ እየሰራ እንደነበረ ሲሆን መሐመድ የአይሁድን ድጋፍ በፈለገበት ጊዜ ስርዓታቸውን መውሰዱን ይህንን ተስፋ ባጣበት ጊዜ ደግሞ ለወጥ አድርጎ መጠቀሙን ነው፡፡ በሁለተኛውና በመለወጡ ሁኔታ ላይ በአጠቃላይ ስርዓቶቹን ወደ ጣዖት አምልኮና የአሕዛብ አረቦች ባህል (ልማድ) ቀይሯቸዋል፡፡
በመሐመዳውያን የቁርአን እግዚአብሔራዊነት ፅንሰ ሐሳብ ላይ ይህ ክስተት ሊብራራ አይቻልም፡፡ በልማድ መሰረት ይህ የሆነው ከሒጂራ ወዲያው ቀጥሎ ነው (በዚህ በኩል ተቀባይነት ያለው መሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም)፡፡ ያም የቁርአን ብዙዎቹ ጥቅሶችና ብዙው ትምህርቱ ከእስራኤል ነቢያት ጋር የማይጋጭ ነው በማለት የሚናገርበት ነው፡፡ ይህም የተያዘው ቁርአን ከእግዚአብሔር ለመሆኑ ዋና ማረጋገጫ እንደሆነ ነው፡፡ የኋለኞቹ የመካና የቀደሙት የመዲና ምዕራፎች አሰሳ እንደሚያሳየው በዚያ ወቅት መሐመድ በምዕራፎቹ ውስጥ እጅግ በጣም ብዙ የሆኑ የአይሁድ አፈ ታሪኮችን ጨምሮበት ነበር፡፡ አይሁዶች የእርሱን ጥያቄ ለመቀበል እንዲሁም በእርሱም የተደነቁ መስለው መታየታቸው ለጊዜው የራሳቸውን ዓላማ የሚያሟላላቸው ቢመስልም ወዲያውኑ በእርሱ ለማመን ዝግጁ አልሆኑም ነበር፡፡ ቆይቶም ይሁን ወዲያውኑ ልዩነት መምጣቱ አልቀረም ምክንያቱም ከእስማኤል ዘር ውስጥ ታላቅ ነቢይ ወይንም መሲህ ይመጣል በማለት እንደተተነበየ ወይንም እንደሚመጣ ማንኛውም እውነተኛ እስራኤላዊ ሊያምን አይችልምና (መሐመድም እንደ ኢየሱስ ማዕረግ ተቀባይነት እንዳለው በእርግጥ አልጠየቀም)፡፡ በመሐመድና በአይሁድ መካከል ጥሉ እንዴት እንደመጣ እናውቃለን፡፡ መሐመድ በእነሱ ዘንድ ተቀባይነት ማግኘት ምንም ጥቅም የሌለው መሆኑን በማወቁ በመጨረሻ አይሁዶች ሊቋቋሙት ወደማይችሉት ሰይፍ መዘዛ ሎጂክ ዞረ፡፡ ከዚያም እረዷቸው ወይንም ከአገር አባሯቸው ወደማለት ደግሞ መጣ፡፡ ነገር ግን ከዚያ ሰዓት በፊት ከእነርሱ እጅግ በጣም ብዙ ነገሮችን ተበድሯል፡፡ ምንም እንኳን ይህንን ባናገኝም በአንዳንድ ጸሐፊዎችና በእስላሞች ዘንድ የሚገኘው የአንድ አምላክ ትምህርት በቀጥታ የተወሰደው ከአይሁድ ትምህርት ላይ ነው፡፡ ስለዚህም መሐመድ ከእስራኤላውያን የተማረውን ትምህርት ይዞ መቀጠሉ ትልቅ ድጋፍ እንደሆነው ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ በመሆኑም በዚህ ምዕራፍ የቁርአን በጣም ብዙው ክፍሉ በቀጥታ ከአይሁድ መጽሐፍ ላይ የተወሰደ መሆኑን በማሳየት እንቀጥላለን፡፡ በእርግጥ ከብሉይ ኪዳን ላይ የተወሰዱት ከታልሙድና ከመጽሐፍ ቅዱስ መጠናቀቅ በኋላ እንደተወሰዱት ብዙ አይደሉም፡፡ የአረቢያ አይሁዶች የራሳቸው ቅዱስ መጽሐፍ ቅጂ ቢኖራቸውም እንኳን በጣም የተማሩ አልነበሩም፣ በአሁኑ ዘመን እንዳለው ሁሉ በዚያን ጊዜም ከእግዚአብሔር ቃል ይልቅ በአብዛኛው ትልቅን ስፍራ ሰጥተውት የነበረው ለራባኒካዊው (ለካህናቱ) ልማዳዊ ትምህርት ነበር፡፡ ስለዚህም በቁርአን ውስጥ እውነተኛና ትክክለኛ የሆነ የብሉይ ኪዳን ትምህርት አለመኖሩ አስደናቂ አይሆንም ማለት ነው፡፡ ሆኖም እንደምናየው ሁሉ ቁርአን እጅግ በጣም ብዙ የሆኑ የአይሁድ አፈታሪኮች ሞልተውበታል፡፡ ይህንን የሚያረጋግጡትን ሁሉንም ክፍሎች መጥቀስ በጣም የማይቻል ነው፣ ነገር ግን ከብዙዎቹ ውስጥ ጥቂቶቹን በዚህ ምዕራፍ ውስጥ እንመለከታቸዋለን፡፡
የአዘጋጁ ማሳሰቢያ፡
ሙስሊሞች ሁሉ ቁርአን በቀጥታ ከእግዚአብሔር የመጣና የመገለጦች ሁሉ የመጨረሻ መገለጥ እንደሆነ ብዙ ይናገራሉ፡፡ በእርግጥ ይህ ትክክል ነውን? ትክክል ለመሆኑስ ማስረጃችን ምንድነው? እና ሌሎችንም ተመሳሳይ ጥያቄዎችን ለሚጠይቅ አዕምሮ ጉዳዩ በቀላሉ የሚታለፍ አይሆንም፡፡ ከዚህ በላይ ያለው ምዕራፍ ሦስት ክፍል አንድ የሚያሳየው ቁርአን የተቀናበረው መሐመድ ነቢይ ነኝ በማለት በተነሳበት ወቅት ከነበሩ የሃይማኖት መጻሕፍት፣ ሃይማኖቶች እንዲሁም አፈታሪኮች ሁሉ ነው ይላል፡፡ የአራቱንም ስምና ዝርዝር በቀጥታ ከቁርአን 22.17 ላይ እንደማስረጃም ያስቀምጣል፡- ‹እነዚያ ያመኑ እነዚያም ይሁዳውያን የኾኑ ሳቢያኖችም ክርስትያኖችም መጁሶችም እነዚያም (ጣዖታትን በአላህ) ያጋሩ አላህ በትንሣኤ ቀን በመካከላቸው በፍርድ ይለያል አላህ በነገሩ ሁሉ ላይ በእርግጥ አዋቂ ነውና›፡፡
በሚቀጥሉት የምዕራፍ ሦስት ተከታታይ ክፍሎች ውስጥ የምናያቸው አስደናቂ ማስረጃዎች የቁርአንን ምንጭ በጣም ግልጥ ባለ መልኩ ያሳዩናል፡፡ በመሆኑም የሙስሊም አንባቢዎችና ሌሎችም ማስረጃዎቹን በጥሞና እንድትመለከቱና እውነታዎቹን እንድታመዛዝኑ በግልጥ ቀርቦላችኋል፡፡ ይህም እውነትን ለማወቅ ለምታደርጉት ጉዞ ትልቅ እርዳታ እንደሚሆንላችሁ እናምናለን፡፡
እንደምናምነው የእምነት ነገር በቸልታ ሊታይ አይገባውም፡፡ ምክንያቱም ከዚህ ዓለም አጭር የቆይታ ዘመን በኋላ ስላለው ዘላለማዊ ሕይወት በቀጥታ የሚመለከት ነውና፡፡ የምከተለው እምነት እውነት ካልሆነ፣ ስለ ዘላለም ሕይወትም የሚሰጠው ምንም ትክክለኛ ተስፋ ከሌለ ምን ይጠቅመኛል? ለምንስ እከተለዋለሁኝ?
መጽሐፍ ቅዱስ ግን በጣም የተለየ ነው፡፡ በሰው ልጅ የዘመናት ታሪክ፣ በግለሰብ የሕይወት ለውጥ በሳይንሳዊም መንገድ እንኳን ተመዝኖ ያለፈና እንከን የሌለው የአምላክ ቃል ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ለሕይወት የሚናገር፣ ተናጋሪ መጽሐፍ ነው፣ ለሚያነቡት ሁሉ የሚገባና ግልፅ ነው፡፡ ስለዚህም በዚህ ድረ-ገፅ ላይ የሚወጡትን ተከታታይ ጽሑፎች እየተከታተላችሁ መጽሐፍ ቅዱስን እንድታነቡ እንጋብዛችኋለን፡፡ እግዚአብሔርም በፀጋውና በፍቅሩ ኃይል ወደ እውነት ሁሉ እንድትመጡ ይርዳችሁ! አሜን፡፡
የትርጉም ምንጭ: THE ORIGINAL SOURCES OF THE QUR'AN
ሙሉ መጽሐፉ በአማርኛ: የቁርአን የመጀመሪያ ምንጮች
ለእስልምና መልስ አማርኛ ዋናው ገጽ