ኢየሱስ ክርስቶስ

M.J Fisher, M.Div.

በአዘጋጁ የተቀናበረ

 መግቢያና ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ንፅፅር

ኢየሱስ ክርስቶስ ነቢይ ብቻ ነው ወይንስ በስጋ የተገለጠ እግዚአብሔር እንደሚለው ጥያቄ ያለ መጽሐፍ ቅዱስን ከቁርአን የለየ ሌላ ምንም ጥያቄ የለም፡፡ በዚህ ምዕራፍ ውስጥ በአጭሩ የተብራሩት (የተገለጡት) ሰማንያ ስምንት የቁርአን ጥቅሶች የእስልምናን አቋም ማዕከላዊ ነጥቦች ግልጥ አድርገው ያሳያሉ፡፡ ክርስትያኖች የሚያምኑት የዘላለም ሕይወትንና ደኅንነትን ለማግኘት ትክክለኛ የሆነ የክርስቶስ መረዳት እጅግ በጣም አስፈላጊ መሆኑን ነው፡፡

የመጽሐፍ ቅዱሳዊው የኢየሱስ ክርስቶስ ማንነት በወንጌል መልክቶች ውስጥ በጣም ግልጥ ነው፡፡ ይህ ጥቅል ጭብጥና ንፅፅር የተሰጠውም በመጽሐፍ ቅዱስ ከቀረበውና በቁርዓን ላይ ከተመዘገቡት ገለፃዎች አንፃር ነው፡፡ የክርስቶስ ሐዋርያት ያስተላልፉት የነበረውን መልክት ማለትም ክርስቶስ መሢህ መሆኑን፤ እንዲሁም ከድንግል የተወለደ ቅዱስ ልጅ መሆኑን፣ ታላላቅ ተዓምራትን ማድረጉን፣ እንዲሁም የከበሩ ሐዋርያት የተከተሉት መሆኑን እና ወንጌልን ያመጣ መሆኑን ሁሉ ቁርአን ማረጋገጡ አስደናቂ ነው፡፡ እንዲያውም ኢየሱስን እንደ እግዚአብሔር ቃልና የአላህ መንፈስም አድርጎ ቁርአን ያውጀዋል፡፡ ምንም እንኳን መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ፤ ባይኖር ቁርአን ኢየሱስ ከሸክላ ሕይወት ያለውን ወፍ እንደፈጠረም ይናገራል፡፡ 

በሌላ በኩል ደግሞ ቁርአን እነዚህ የተጠቀሱት ተዓምራትና የከበሩ ስሞች በሙሉ የኢየሱስን በስጋ የተገለጠ አምላክነት ማሳየታቸውን ይክዳል፡፡ የሚያውጀውም ኢየሱስ የአላህ ባሪያ በመሆን አላህን ልክ መሐመድ እንዳገለገለ ብቻ አገልግሏል ነው የሚለው፡፡ ከዚያም የበለጠ በመሄድ የቅዱስ ስላሴን እምነት፣ የኢየሱስ ክርስቶስን መሰቀል እንዲሁም የእግዚአብሔር ልጅ ነው የሚለውንም መጠሪያ ይክዳል፡፡ ሙስሊሞች ‹የእግዚአብሔር ልጅ› የሚለው አጠራር አላህ ልጅ ለማግኘት የግብረ ስጋ ግንኙነት እንዳደረገ የሚገልጥ አባባል ነው በማለት ይነቅፉታል፡፡ ይህንን የተሳሳተም መረዳት ክርስትያኖች ሲያገኙትም እጅግ በጣም ይረበሻሉ፡፡

እስላሞች የክርስቶን ስቅለት መካዳቸውንም በዚህ ትንሽ መግለጫ ውስጥ መጥቀሱ እጅግ በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ ቁርአን በኢየሱስ ክርስቶስ የመስቀል ስራና የትንሳኤ እምነት ስለሚገኝ የዘላለም ደኅንነት ምንም የሚናገረው ነገር የለውም፡፡ የሚናገረውም አይሁዶች መሢሁን እንዳልገደሉት ነው የመሰለውም (አላህ እራሱ ያስመሰለው) ለእነሱ እንደገደሉት ብቻ ነው ነገር ግን አላህ እሱን ወደ እራሱ ወሰደው፡፡ ይህ ምን ማለት ነው? የሙስሊም ትራዲሽን እንደሚለው ይሁዳ በተዓምራት ኢየሱስን መስሎ በመለወጥ ተሰጥቶ በእሱ ምትክ፣ አይሁዶች ይሁዳ ኢየሱስን መስሏቸው እንደሰቀሉት ነው፡፡ ይህም ኢየሱስ በምስጢር ወደ አላህ ተወስዶ ነው፡፡ በዚህ መንገድ እሱ አጥቅተው ሊገድሉት ከነበሩት ከወገኖቹ ከአይሁዶች አምልጧል፡፡ (እንግዲህ የዚህ የኢየሱስ ከመሰቀል የመዳንና የማምለጥም ሴራ አቀናባሪው ደግሞ እራሱም አላህ ሆኖ ተቆጥሮ ነው)፡፡

የሚከተሉትን ጥቅሶች ከቁርአን ውስጥ ካጠናን በኋላ ዋናና ማዕከላዊ ጥያቄ ይቀራል፡፡ ቁርአን ትክክል ከሆነ የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮች ወደ ዓለም ሁሉ በመሄድ ለምንድነው የኢየሱስ ክርስቶስን ሞትና ትንሳኤ ምስክሮች እንደሆኑ ያወጁትና ይህንንም ለሚያምኑት ሁሉ ደኅንነትን እንደሚያገኙ የሰበኩት? እንዲሁም እነሱ ይህንን ያመኑቱ እና የተለወጡቱ በአንድ አምላክ ስም፣ ማለትም በአብ በወልድ እና በመንፈስ ቅዱስ ስም እንዲጠመቁ ለምን አዘዙ? መልሱም የሚሆነው ሙስሊሞች የመጀመሪያው ወንጌል በታሪክ ውስጥ ሲተላለፍ እንደተለወጠ እንደሚያምኑ ነው፡፡ ስለዚህም ሙስሊሞች የሚያምኑት እውነተኛዋን ቤተክርስትያን ለመመስረት የኢየሱስ ተልዕኮ እንዳልተሳካ ነው፡፡ ታዲያ በመሐመድ ዘመን የነበረችው የአረቢያ ባህረሰላጤ ቤተክርስትያን የኢየሱስን ወንጌል መልክት እንዴት ነበር የተቀበለችው?

የመሐመድ ዘመን ቤተክርስትያን ቁርአንን አልተቀበለችውም ምክንያቱም መልእክቱ ክርስቶስ ኢየሱስን ያቃልል ነበርና፡፡ ከሐዋርያት ጀምሮ አዲስ ኪዳን በግልጥ የሚያስተምረው ኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ ሰው ነገር ግን የእግዚአብሔር ቃል እንደበር፣ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር (አማኑኤል)፣ የማይታየው አምላክ ምሳሌ፣ ከአብ ጋር አንድ የሆነ ፍፁም አምላክ፣ በእሱም የእግዚአብሔር ሙላቱ በእውነተኛ የሰው አካል ውስጥ የሚኖርበት እንደሆነ ነው፡፡ ይህ እጅግ ጠቃሚ ነው ምክንያቱም ሐዋርያቱ በሙሉ ኢየሱስ ሰው እንደበረ ያውቁ ነበር፡፡ ደግሞም ለሰዎች ልጆች ኃጢአት (ፍርድ) መስዋዕት ሆኖ ዋጋ ለመክፈል የመጣ ፍፁም አምላክም እንደሆነ ያምኑ ነበር፡፡ በዚህ መንገድም የሰውን ልጆች ኃጢአት ዋጋ ከፈለ፣ ነገር ግን እሱ ፍፁም መለኮት አምላክ ነበረ እንዲሁም ደኅንነትን ለማስገኘት የሚበቃ ፍፁም ቅዱስ ነበረ፡፡ ይህ ደግሞ እነሱ ዝም ብለው የፈጠሩት የፈጠራ ታሪክ አልነበረም በብሉይ ኪዳንም ነቢያት ትንቢት ውስጥ ለእነሱ ተገልጦላቸው ነበር (መዝሙር 22፣ ኢሳያስ 53) በመላእክት (ማቴዎስ 1.20-25) በመጥምቁ ዮሐንስ (ዮሐንስ 1.29) በጌታ በኢየሱስ በራሱ (ሉቃስ 24.44-53) እንዲሁም በሐዋርያቱ (ቆላስያስ 1.15-20)፡፡

ጌታ ኢየሱስ በመጨረሻው ዘመን እሱ በመላእክት ታጅቦ እንደሚመጣ ተናገሯል እንዲሁም በዙፋኑ ላይ ተቀምጦ በሕዝብ ላይ ይፈርዳል (ማቴዎስ 25. 31-32)፡፡ እጅግ በጣም በቁጣ የተሞሉት፤ በአንድ አምላክ እናምናለን የሚሉት እና እሱን ይሰሙት የነበሩት አይሁዶች ማድረግ የነበረባቸው መለኮት ስለሆነ የሚናገረውን አምኖ መቀበል ወይንም ደግሞ መለኮትን የሰደበ ሰው ስለሆነ መገደል ያለበት አድርገው ነበር፡፡

በዘመናት ሁሉ የነበሩት ክርስትያኖች በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት አምነው፣ ኢየሱስ የተናገረውን ነገር የነበረ ሰው እንደሆነ እና የእሱንም የወንጌል መልክት (የምስራቹን ቃል) ለማወጅና ለማስፋፋት የራሳቸውንም ሕይወት በአደጋና በመስዋዕትነት ውስጥ እየጣሉ ማወጅን ነበር፡፡ የኢየሱስ ቤተክርስትያን ወደ ፊት እያደገች ብዙዎችን እየደረሰች፣ እየደረሰች እንደትሄድ ያደረጉት የእሱን ቃሎች አምነው ነበር፡፡ ስለዚህም የገሃነም (የሰይጣናት ኃይሎች) ደጆች ይህንን እንቅስቃሴ ሊያግዱት በፍፁም አልቻሉምም ነበር፡፡

ስለዚህም ጌታ ኢየሱስን በተመለከተ ቁርአን የሚከተለውን ይናገራል፡-

ቅዱስ፣ መገለጥ እና ምህረት፡-

የአላህ መንፈስ ልክ ሙሉ ለሙሉ እንዳደገ ትልቅ ሰው ለድንግል ማርያም በተገለጠበት ጊዜ ያወጀላት ነገር ቅዱስ የሆነ ወንድ ልጅ እንደሚኖራትና እሱም ለሰው ልጅ መገለጥ እንደሚሆንና ከአላህም ዘንድ ምህረት እንደሚሆን ነው 19.17-21፡፡ ‹እኔ ንፁሕን (ቅዱስን) ልጅ ለአንቺ ልሰጥሽ የጌታሽ መልክተኛ ነኝ አላት፡፡ (በጋብቻ) ሰው ያልነካኝ ኾኜ አመንዝራም ሳልኾን ለኔ እንዴት ልጅ ይኖረኛል አለች እሱም አላት፡- (ነገሩ) እንደዚህሽ ነው፣ ጌታሽ፡- እርሱ በእኔ ላይ ገር ነው ለሰዎችም ታምር ከኛም ችሮታ ልናደርገው (ይህንን ሠራን) የተፈረደም ነገር ነው አለ (ነፋባትም)፡፡›

ሥላሴ የሚባል ነገር የለም፡-

የመጽሐፉ ሰዎች ስለ አላህ ሲናገሩ ምንም ማጋነን አይኖርባቸውም፡፡ መሲሁ ኢየሱስ የማርያም ልጅ የአላህ መልክተኛ ብቻ ነው፣ ቃሉ ነው ለማርያም የተሰጠ ከእሱ የሆነ መንፈስ ነው፡፡ ስለዚህም በአላህ እና በመልክተኞቹ እመኑ እናም ‹ሦስት› ናቸው ብላችሁ ማለትን አቁሙ፡፡ አላህ አንድ ብቻ ነው፡፡ እሱ ልጅ ሊኖረው የማይችል ታላቅ እና የተለየ ነው፡፡ መሲሁም የአላህ ባሪያ ለመሆን አያፍርም 4.171፣172፡፡

የአላህ እስትንፋስና መንፈስ፡-

የኢምራም ሴት ልጅ ማርያም ንፅህናዋን የጠበቀችው የጥሩ ሚስት ምሳሌ ናት፡፡ አላህም በአላህ ውስጥ መንፈሱን ተነፈሰባት (የኢየሱስ መፀነስ) እናም እርሷ እውነቱን መሰከረች (ያማረ የድንግል መውለድ የነበረ መሆኑን) 66.12፡፡

ከታዘለበት አንቀልባ ላይ ሰበከ፡-

በፍርድ ቀን አላህ ኢየሱስን ከሌሎች ጋር ሐዋርያት የነበረውን ኢየሱስን ጥያቄ ይጠይቃል፡፡ አላህም ኢየሱስን የሚጠይቀው በመንፈስ ቅዱስ ምን ያህል ጥንካሬ እንደተሰጠው ያስታውስ እንደሆነ እና እንደታዘለ በነበረበት ጊዜ እንዴት እንዲሰብክ እንደተደረገም (የእናቱን ንፅህና በተመለከተ ማስረጃን በሰጠበት ጊዜ) እንዲሁም ልክ እንደ ሰው በነበረበት ጊዜ (5.110)፡፡

የሕፃኑ አዋጅ፡-

እንደ ሕፃን ኢየሱስ በተዓምራት የተናገረውና ያወጀው ወንጌል የሰጠው የአላህ ባሪያና ነቢይ እንደሆነ ነው፡፡ ሕፃኑ ኢየሱስ አላህ ንፁህ እንዳደረገውና እንዲፀልይ እንዲሁም ምፅዋትን እንዲሰጥና ለወላጆቹም እንዲታዘዝ እንዳዘዘው ተናግሯል (19.29-33)፡፡

የእግዚአብሔር ልጅ አይደለም፡-

ኢየሱስ የማርያም ልጅ ነው፡፡ ክርስትያኖች ሊያምኑት የማይፈልጉት አጠቃላይ ታሪክ ይህ ነው፡፡ አላህ ልጅ አለው ብሎ ማሰብ አላህን ዝቅ ማድረግ (ማቃለል) ማለት ነው፡፡ አላህ ዝም ብሎ ነገሮችን እንዲሆኑ ያዛል እነሱም ይሆናሉ (ይህም ኢየሱስ ከድንግል እንደተወለደው ማለት ነው) 19.34፣35)፡፡ አላህ ወንድ ልጅ እንዳለው የሚናገሩት እነዚያ የሚያውጁት እጅግ ጥፋትን ነው፡፡ ለአላህ ልጅ አለው በማለት የሚናገሩ ከሆነ ሰማይ ይሰነጠቃል ምድርም ትከፈላለች ተራሮችም ይወድቃሉ፡፡ ይህ ለእሱ ክብር የሚገባ አይደለም 19.88-92፡፡ አላህ ልጅ አለው በማለት የሚያምኑት እነሱ ውሸታሞች ናቸው እንዲሁም ይቀጣሉ 10.68፣69፡፡ መሐመድም እንዲናገር ተነግሮት የነበረው አላህ ልጅ ቢኖረው እሱ ሊያመልከው የመጀመሪያው እንደሚሆን ነበር፡፡ ክርስትያኖች በፍርድ ቀን መልስን የሚሰጡበት ውሸት ነው 43.81-83፡፡ አላህ ምንም ልጆች የሉትም ወይንም በሰማይ መንግስቱ ውስጥ ሚስት የለውም 25.2፡፡

ባሪያ ብቻ፡-

የማርያም ልጅ እንደምሳሌ በታወጀበት ጊዜ (በሰው መልክ የተገለጠ ታላቅ አምላክ) ጣዖት አምላኪዎች ያሾፉትና የተከራከሩት ከእነሱና ከኢየሱስ የሚሻለው ማን ነው በማለት ነው፡፡ ኢየሱስ አላህ ፀጋ የሰጠው እና ለእስራኤል ልጆች ምሳሌ (ነቢይ) ያደረገው ባሪያ ብቻ እንጂ ሌላ አይደለም፡፡ ኢየሱስም የመጣው በግልፅ ተዓምራት ሲሆን ለሕዝቡም የነገራቸው ለአላህ የሚገባቸውን ነገር እንዲያደርጉና እንዲታዘዙት ነው፡፡ እሱም ለሕዝቡ ያዘዛቸው አላህን የእነሱንና የእሱን ጌታ እንዲያመልኩ ነው 43.57-64፡፡

በመንፈስ ቅዱስ ተጠናክሯል፡-

የማርያም ልጅ ኢየሱስ ተዓምራትን እንዲሰራ ኃይል ተሰጥቶት ነበር እንዲሁም በመንፈስ ቅዱስ ጥንካሬ ተሰጥቶት ነበር፡፡ ነገር ግን ሐዋርያው ባልተጠበቀ ትምህርት ሲመጣ አይሁድ ትዕቢተኞች ሆኑና ከፊሎቹን አስተባበሉ ከፊሉንም ገደሉ 2.87፣253፡፡

ምንም አዳኝ የለም፡-

እያንዳንዱ (ኢየሱስን ጨምሮ) በፍርድ ቀን በአላህ ፊት ይቀርባል ይህም እንደ ባሪያ ያለምንም አዳኝና አማላጅ በመሆን ነው 19.93-95፡፡

ቶራን ደግፏል እንዲሁም መሐመድ እንደሚመጣ ተንብዮአል፡-

ኢየሱስ የመርያም ልጅ ለእስራኤል የተናገረው ከእርሱ በፊት የወረደውን የአይሁድን ቅዱስ መጽሐፍ ለማረጋገጥ እንደሆነና እንዲሁም ከእርሱ በኋላ የሚመጣውን እና አህመድ የተባለውን ሐዋርያ ለማብሰር ነው 61.6፡፡

ደቀ መዛምርቱ፡-

አንዳንድ አይሁዶች ኢየሱስን እንደ አላህ አጋዦች በመሆን ተከተሉት ስለዚህም እነሱ በጠላቶቻቸው ላይ እንዲያሸንፉ ተባረኩ 61.14፡፡ የኢየሱስ ደቀመዛምርት ለአላህና ለሐዋርያው ለኢየሱስ እራሳቸውን አስገዙ፡፡ እነሱም አማኞችና መስካሪዎች ነበሩ፡፡ አላህም ኢየሱስን ከጠላቶቹ ነፃ ለማውጣት ወደ እራሱ ካነሳው በኋላ ደቀመዛምርቱ ተባርከው ነበር፡፡ የኢየሱስን ተከታዮች ከማያምኑት በላይ ከፍ ተደርገው ተባርከዋል ይህም እስከ ትንሳኤ ቀን፣ የሃይማኖት ክፍፍል እስከሚወገድበት ድረስ ነው 3.55፡፡

ተዓምራትን ሰርቷል፡-

ኢየሱስ የመጣው በግልጥ ምልክቶች ነበር ነገር ግን ሰዎች እንደ ጠንቋይ (በመቁጠር) አልተቀበሉትም ‹...  በግልፅ ምልክት በመጣቸውም ጊዜ ይህ ግልፅ ድግምት ነው አሉ› 61.6፡፡ በአላህም ፈቃድ ኢየሱስ የሸክላ ወፍን ሕይወት ዘርቶባታል ለእውርም ማየትን ሰጥቷል ለምፃምን ፈውሷል እንዲሁም ሙታንን ወደ ሕይወት መልሷል 3.49፡፡

የክርስቶስ መሰቀል፡-

አይሁዶች ቃል ኪዳኑን አፈረሱ፣ የአላህን መገለጥ ክደው ነቢያትን በግፍ ገደሉ፡፡ በማርያምም ላይ እጅግ አስፀያፊን ስድብ ይናገራሉ፡፡ እንደዚሁም መሲሁን የአላህን መልክተኛ የማርያምን ልጅ ኢየሱስን ገደልነው አሉ፡፡ እነሱ አልገደሉትም ወይንም አልሰቀሉትም፡፡ እንደተሰቀለ መስሏቸው ብቻ ነበር፡፡ አልገደሉትም ግን አላህ ወደ እራሱ ወስዶት ነበር 4.155-158፡፡ አላህ ኢየሱስን እንዲሞት ካደረገው በኋላ (ወይንም ሳይሞት እንዲያርግ ካደረገው በኋላ) ወደ ሰማይ አነሳው ከጠላቶቹ ከማያምኑት ሊያድነው ደቀመዛምርቱም ተባርከው ነበር፡፡ የኢየሱስም ተከታዮች እስከ ትንሳኤ ቀን ድረስ ከማያምኑት በላይ ይከበራሉ በመካከላቸው ያለው ክርክር በሚፈረድበት ጊዜ 3.55፡፡

ከሸክላ፤ ሕይወት ያላትን ወፍ ሰርቷል፡-

በፍርድ ቀን አላህ ከሌሎች ሐዋርያት መካከል የሚሆነውን ኢየሱስን እንዲህ በማለት ይጠይቀዋል፡፡ እሱም የሚጠየቀው እንዴት የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች እንደተሰጠውና የጥበብ እና የተዓምራት ኃይል እንደተሰጠው ያስታውስ እንደሆነ ነው፡፡ በአላህ ፈቃድ ወፍን ከሸክላ (ከጭቃ) ሰራ እና ሕይወትን ተነፈሰባት (ሕይወት እንዲኖራት) 5.110፡፡

የጠረጴዛ ምግብ ከሰማይ፡-

በፍርድ ቀን ከሌሎች ሐዋርያት ጋር የሚሆነውን ኢየሱስን አላህ ይጠይቀዋል፡፡ እሱም ዕውር ሆኖ የተወለደውን በአላህ ፈቃድ እንዴት ዓይኑን እንዳበራው ለምፃሙን እንዴት እንደፈወሰው እና የሞተውን እንዴት እንዳስነሳው ይጠይቀዋል፡፡ ኢየሱስ ለተከታዮቹ ከሰማይ ምግብ የነበረበትን ጠረጴዛ እንዲጠራው የተፈቀደበትን ታሪክ እንዴት እንደተደረገ ይናገራል 5.110-115፡፡

ሥላሴን መካድ፡-

በፍርድ ቀን ከሌሎች ሐዋርያት ጋር የሚሆነውን ኢየሱስን አላህ ይጠይቀዋል፡፡ ኢየሱስም ለሰዎች ልጆች እሱን እናቱንም ከአላህ ጎን እንደሁለት አምላኮች እንዲያመልኳቸው ተናግሮ (አስተምሮ) እንደሆነ ይጠየቃል፡፡ ኢየሱስም ይህንን እጅግ በጣም አድርጎ ይክዳል 5.116-118፡፡

ኢየሱስ ልክ እንደ አዳም ነው፡-

አዳምና ኢየሱስ ሁለቱም በአላህ ትዕዛዝ ልዩ ፍጡሮች ናቸው 3.59፡፡ (ይህ እጅግ አስደናቂ ጥቅስ ነው ምክንያቱም ቁርዓን የኢየሱስን መመለክ ይክዳልና ነገር ግን ሰይጣን ወደ ገሃነም (ሲዖል) እንዲጣል የተደረገው አላህ ለአዳም ስገድ ባለው ጊዜ እምቢ በማለቱ ነበር፣ አዳም ደግሞ ከአፈር (ከሸክላ) የተቀረፀና ሕይወት የተሰጠው ነበር፡፡ ሰይጣን አላህ እንዲህ ዓይነትን ነገር እንዲያደርግ እንደሚጠይቀው አላመነም ነበር ምክንያቱም ኢሎጂካል ነበርና፡፡ የዚህ የሰይጣን ታሪክ በሚከተሉት ጥቅሶች ውስጥ ነው የሚገኘው (7.11-23፣15.28-39፣ 18.50፡፡)

የአዘጋጁ ማሳሰቢያ፡-

ከዚህ በላይ ባየናቸው ሰማንያ ስምንት የቁርዓን ጥቅሶች ውስጥ ሙስሊሞች ስለጌታ ኢየሱስ ያላቸው ግንዛቤ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር በፍፁም የተቃረነ ነው፡፡ የጌታ ኢየሱስን ማንነት ለመረዳት የሚፈልግ ማናቸውም ሰው ጥናቱንና ወይንም ንባቡን መጀመር ያለበት ከታሪኩ ምንጭ ከወንጌሎችና ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ነው፡፡ ጌታ ኢየሱስ ማነው? ክርስትያኖች ስለ እሱ ያላቸውን መረዳት ከየት ነው ያገኙት? ጌታ ኢየሱስን ክርስትያኖች እንደሚያምኑት ለመከተልና ለማመን ምን ያስፈልጋል? በጌታ በኢየሱስ ማመን ምን ይጠይቃል? የመሳሰሉትን ለመረዳት መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ጀምሩ እግዚአብሔር በቃሉ ውስጥ እራሱንና ለሕይወታችሁ ያለውን እውነተኛ ዕቅድ ግልፅ ያደርግላችኋል፡፡ እግዚአብሔር ይርዳችሁ፡፡

 

የትርጉም ምንጭ: Jesus Christ, Chapter 21 of "A Topical Study of the Qur'an From a Christian Perspective" by M.J Fisher, M.Div

ሙሉ መጽሐፉ በአማርኛ: ርእሳዊ የቁርአን ጥናት በክርስትና አይን ሲመረመር

 

ለእስልምና መልስ አማርኛ  ዋናው ገጽ