ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በእርግጥ አምላክ ነውን?

በአዘጋጁ

 

ኢየሱስ አምላክ ነኝ በእርግጥ ብሏልን ካለ ይህንን እስኪ አሳየኝ?

ይህ ጥያቄ በተደጋጋሚ በሙስሊሞች የሚቀርብና የተለመደም ነው፡፡ ጥያቄውን የጂሆቫ ዊትነስ ተከታዮችም ለየት ባለ መልኩ ያነሱታል፣ እነርሱም በጌታ በኢየሱስ አምላክነት ከማያምኑት ወገን ናቸው፡፡ የዛሬው ትኩረታችን ወደ ሆነው ወደ ሙስሊሞች ስንመጣ ብዙ ሙስሊሞች ይህንን ጥያቄ በክርስትያኖች ላይ የሚወረውሩት የክርስትያኖች እምነት ስህተትና ጭፍን እንደሆነ አምልኳቸውም የተዛባና መታረም እንዳለበት ገምተው ነው፡፡ የጂሆቫ ዊትነሶች ሲናገሩ እንደሚደመጡትና እንደሚያስቡት ሁሉ ሙስሊሞችም ለጥቄያቸው መልስ የሌለው ይመስላቸዋል፡፡

የጌታ ኢየሱስን አምላክነት በተመለከተ ሙስሊሞች ለሚያነሱት ለዚህና ለተመሳሳይ ጥያቄ ትክክለኛ ይቺ ጽሑፍ መልስን ትሰጣለችና በቅንነትና በጥንቃቄ ልናነባት ይገባናል፡፡

የሙስሊሞቹ ጥያቄ፡- ‹ነቢዩ ኢየሱስ ወይንም ኢሳ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የትም ቦታ ላይ አምላክ ነኝና አምልኩኝ አላለም፡፡ ስለዚህም እናንተ ክርስትያኖች ኢየሱስን አምላክ ነው የምትሉት መሰረት የሌለው ነገር ነው፤ ከመጽሐፍ ቅዱሳችሁም ላይ ማረጋገጥ አትችሉም› የሚል ነው፡፡

ይህንን ጥያቄ በእርጋታ መመርመር አስፈላጊ እንደሆነ ማመን አለብን፡፡ እኛ ክርስትያኖች አምላክ እንደሆነ የምናምነው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ እኔ አምላክ ነኝና አምልኩኝ ብሎ ለመናገር ችግር ነበረበትን? የሚለውን ጥያቄ ብንጠይቅ የምናገኘው መልስ በፍፁም እርሱ ችግር አልነበረበትም የሚለው ነው፡፡ ታዲያ ችግሩ የት ነበር? በእርግጥ በአሁኑም ዘመን እንዳለው ሁሉ ችግሩ የነበረው በሰዎች አመለካከትና እምነት ላይ ነበር፡፡

በሰዎች አመለካከትና እምነት ላይ የነበረውን ችግር ለመረዳት የሚከተለውን ሐሳብ መመልከት በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ እንበልና አንድ ሰው ወደ እናንተ መጥቶ፡ ‹በእርግጥ እኔ አምላክ ነኝ እና አምልኩኝ› በማለት ጥያቄ ቢጠይቃችሁ እናንተ ምን ትላላችሁ? በእርሱ ታምናላችሁን፣ እርሱንስ ታመልኩታላችሁን?

አንድ አምላክ ብቻ እንዳለና እርሱንም የምታመልኩ ብትሆኑ፤ አንድ ሰው ከዚህ በላይ እንደተጠቀሰው ዓይነት ጥያቄን እያቀረበ ማለትም አምላክ ነኝና አምልኩኝ እያለ ብታገኙት ምላሻችሁ ምንድነው? ወዲያውኑ ትቀበሉታላችሁን? በእርግጥ የናንተ ፈጣን ምላሽ የሚሆነው ምንድነው? እውነተኛውን ፈጣሪና ሕግጋቶቹን እንደሚያውቅ እንደ ማንኛውም ሰው የእናንተ አመለካከትና ምላሽ የሚሆነው እንዲህ ዓይነቱን ጥያቄ ያነሳው፣ አምላክን የሚሳደብና አሳሳች ሰው መሆን አለበት የሚል ነው፡፡ ታዲያ የእናንተ ምላሽ እንደዚህ የሚሆን ሆኖ እያለ በወቅቱ ተቀባይነት ያልነበረውን ነገር እንዲናገር ጌታ ኢየሱስን የምትጠብቁበት ለምንድነው?

ብዙዎች እንደዚህ ዓይነት ነገርን ማለትም እኔ አምላክ ነኝ የሚለውን ጥያቄ የሚያነሳውን ሰው ዕብድ ነው ብለው ሊጠሩት ይችሉ እንደነበረ ምንም ጥርጥር የሌለው ነገር ነበር፡፡ በመሆኑም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲህ ዓይነት ምላሽ ሊኖር እንደሚችል፣ እንደዚህ ዓይነት ጥያቄዎችን ማቅረብ ሞኝነት እንዲያውም እግዚአብሔርን መስደብ ተደርጎ እንደሚቆጠር ያውቅ ስለነበር እንዲህ ዓይነትን ጥያቄ አላቀረበም፡፡

በጣም የሚገርመው ነገር እርሱ እንዲህ ዓይነት ጥያቄን ሳያቀርብ፣ አምላክ ነኝና አምልኩኝ ሳይል፣ ሰዎች እርሱን ያመልኩት እንደነበረ እንዳመለኩት አሁንም እያመለኩት እንደሆነ ግልጥ ማስረጃዎች ያሉን መሆኑና ማየታችንም ነው፡፡ እኛም እራሳችን በሕይወታችን ትርጉም ያለውን ስራ ከመስራቱ የተነሳ እርሱ አምላክ እንደሆነ አውቀን ማምለካችን ትክክለኛ ነገር ነው፡፡ ታዲያ እርሱ አምላክ ተደርጎ ለመመለኩ የሚሰጠው ምክንያት ምንድነው? ለዚህ ጥያቄ መልስ የሚሆነው የሚከተለው አስገራሚ ዘገባ ነው፡፡

ጌታ ኢየሱስ እግዚአብሔር መሆኑን በግልጥ አቅርቧል

ጌታ ኢየሱስ አምላክ መሆኑን እጅግ በጣም ግልጥ በሆነ መንገድ አቅርቦታል፡፡ ይህንንም ያደረገው ሰሚዎቹና ተመልካቾቹ ያለምንም ጥርጥር በሚገባቸው ነገር ግን በተዘዋዋሪና እጅግም ግልጥ በሆነ መንገድ ነበር፡፡

እናንተ ሰፊ ልብና ንቁ አዕምሮ ካላችሁ ይህ የእሱ የአምላክነት ማስረጃ አቅርቦት ነገሩን ጠጋ ብላችሁ እንድታዩ የሚያደርጋችሁ መሆን አለበት እንጂ ይህን አሳብ አንቀበልም ብላችሁ በጭፍን እንድታልፉት አያደርጋችሁም፡፡

በዚህ እውነታ ላይ በጣም የሚያሳስበውና ልንመለከተው የሚገባን ነገር እርሱ አምላክ ነኝና አምልኩኝ በማለት የተናገረው ቃል ወይንም አረፍተ ነገር መኖር አለመኖሩን አይደለም፡፡  ነገር ግን እርሱ በእርግጥ አምላክ የነበረ ለመሆኑ ግልፅ ማስረጃዎች መኖር ወይንም አለመኖራቸው ላይ ነው፡፡

እርሱ አምላክ መሆኑን የሚያስረዳ ግልፅ ማስረጃ ካለ ደግሞ እናንተም ፍጥረትም ሁሉ ሊያመልከው ያስፈልገዋል ማለት ነው፡፡ ይህም እርሱ የተናገራቸው ቃላት እናንተ በእርግጥ በትክክል ሊል የፈለጋችሁትን ባይልም እንኳን ነው፡፡ በእርግጥ እግዚአብሔር እራሱን እንዴት መግለጥ እንዳለበት እኛ ሰዎች ሐሳብን ልንሰጥና ወይንም በግምታችን እንደዚህ መሆን አለበት በማለት ለመናገር አንችልም፡፡ ልናደርግ የሚገባን ነገር አምላክነቱን ሊገባን በሚችል መንገድ እርሱ በራሱ መንገድ ገልጧል ወይንስ አልገለጠም የሚለውን መረዳት ነው፡፡

ለምሳሌም ያህል በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ ጌታ ኢየሱስ ስለዘላለም ሕይወት ሲናገር እንደሚከተለው አለ፣ ‹እኔ ትንሳኤና ሕይወት ነኝ በእኔ የሚያምን ቢሞትም እንኳን ሕይወት አለው› ዮሐንስ 11.25፡፡ በዚህ ጥቅስ ውስጥ እርሱ የዘላለምን ሕይወት ስጦታ ሰጪ እንደሆነ እራሱን ‹እኔ› በማለት አቀረበ፡፡ ይህም የዘላለም ሕይወት ስጦታ በእርሱ ላይ በመታመን የሚገኝ መሆኑንም በግልጥ ተናገረ፡፡ ይህንን አቀራረብ በትክክል ረጋ ብለን ብንመለከተው እርሱ እግዚአብሔር ካልሆነ በስተቀር ማንም ሊናገረው አይችልም፣ አይሁዶች እንደሚያምኑትም እንዲህ ዓይነቱን ቃል የሚናገር ሰው በእርግጥም እግዚአብሔርን እየተሳደበ ነው፡፡ እንድ ሰው ሕይወትን ለዚያውም የዘላለም ሕይወትን መስጠት እችላለሁ በማለት ሊናገር ይችላልን? ማንም ሰው መናገር የፈለገውን ሁሉ ለመናገር ይችላል፣ ነገር ግን የሚናገረውን በተግባር ማሳየት ይችላልን? እነዚህ እጅግ በጣም መሠረታዊና አስፈላጊ ጥያቄዎች ናቸው፡፡

ጌታ ኢየሱስ ለተናገራቸው ነገሮች አንዳች ማስረጃን ለማቅረብ ይችላልን? የዮሐንስ ወንጌል ጌታ ኢየሱስ ይህንን በተናገረበት ክፍልና በተናገረበት ቀን ስለሆነው ነገር ዝርዝር ማስረጃዎችን ያቀርባል፡፡ በዝርዝሩም በስተመጨረሻ የምናነበው ነገር እንደሚከተለው የሚል ነው፤ ‹ይህንን በተናገረበት ጊዜ ኢየሱስ በታላቅ ድምፅ ጮኾ ‹አልዓዛር ና ውጣ አለ› የሞተውም ሰው እጁና እግሩ እንደተገነዘ ወጣ፣ ኢየሱስም ለእነሱ ፍቱትና ይሂድ አላቸው›› ዮሐንስ 11.43-44፡፡ ይህ በሆነበት ዕለት ብዙ አይሁዶች በእርሱ አምነዋል፣ እርሱ የተናገረውን የሚያደርግ፣ በመካከላቸው ሰው በመሆን የተመላለሰ፣ ነገር ግን አምላክ ብቻ የሚያደርገውን ነገር አድራጊና እራሱ አምላክ እንደሆነ አረጋግጠው አምነዋል፡፡ ይህ የአንድ ክስተት ማስረጃ ነው፡፡ አምላክ ነኝ ብሎ መናገር ሳያስፈልገው አምላክ መሆኑን ጌታ ኢየሱስ በስራው ግልጥ በሆነ ሁኔታ ይገልጥ ነበር፡፡ እንደዚህ ዓይነት ማስረጃዎች በወልጌሎች ሁሉ ውስጥ በብዛት ይገኛሉ፡፡ እንግዲህ ወንጌሎችን በጥንቃቄ ስታነቡ ፍፁም በሆነ ወጥነት የምታስተውሉት ነገር ቢኖር የሚከተሉትን ጭብጥ ሐሳቦች ነው፡ 

ሀ. ጌታ ኢየሱስ ይናገር የነበረው፣ አምላክ ይናገር እንደነበረ መሆኑን፡፡

ለ. ጌታ ኢየሱስ ይሰራ የነበረው አምላክ ይሰራ እንደበረ መሆኑን፡፡

ሐ. ጌታ ኢየሱስ ለተናገራቸው ነገሮች ሁሉ ትክክለኛ ማንነቱን ይገልጡ የነበሩ ስራዎችን በማስረጃነት እየሰጠ የነበረ መሆኑን ነው፡፡

መ. ጌታ ኢየሱስ የተናገራቸውንና የሰራቸውን ያዩና በቦታው የነበሩ ሁሉ አምላክ መሆኑን በትክክል አውቀው ያመልኩት እንደነበረ፡፡

ሠ. ጌታ ኢየሱስ አምላክ መሆኑን በስራው ያዩ ያቀረበለትን አምልኮ እርሱ ሳይቃወም ይቀበል እንደነበረ ነው፡፡

ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በሚያስተምርበት ጊዜ፣ ከትምህርቶቹ ወይንም ከንግግሮቹ ቀጥሎ ከሚያደርጋቸው ተዓምራቶቹ ደቀመዛምርቱንም ሆነ በዙሪያው ያሉትን ሰዎች እንዲገነዘቡ ይጠብቅባቸው የነበረው ነገር እርሱ ማን እንደሆነ እንዲረዱ ነበር፡፡ ምክንያቱም እርሱ ይናገር የነበረውንና ያደርግ የነበረውን ነገር ሊያደርግ የሚችለው እግዚአብሔር ብቻ ነበርና፡፡ ጌታ ኢየሱስ አምላክ መሆኑን የሚያሳዩ ብቁ ማስረጃዎችን ሰጥቶ ሰዎች እራሳቸው የራሳችሁን ውሳኔ እንዲወስኑ ይተዋቸው ነበር፡፡

በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 20.28 እንዲሁም በማቴዎስ ወንጌል በምዕራፍ 28.16 ላይ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አምልኮን ሲቀበል እንመለከተዋለን፡፡ አምልኮ መቀበል ማለት ደግሞ አምላክ ነህ ሲባል ትክክል ነው አምላክ ነኝ ማለትን በግልጥ የሚያሳይ፣ የእርሱንም አምላክነት በትክክል የሚያስረዳና የሚያረጋግጥ ነው፡፡ እርሱ አምልኩኝ በማለት ባይናገርም እንኳን የእርሱን አምላክነት አውቀው ያመለኩትን ሲቃወማቸው አንመለከትም ምክንያቱም አምላክን ያወቁ ሁሉ ሊያመልኩት ይገባቸዋልና፡፡

አንድ ሰው እኔ እግዚአብሔር ነኝ በማለት እራሱን ሊሰይም ይችል ይሆናል፡፡ ብዙዎችም እራሳቸውን ‹አምላክ› ነን ብለው እንደጠሩ በታሪክ ሁሉ ውስጥ ተመዝግቦ እናገኛለን፡፡ አምላክነት በእጅ ብልጫ፣ በተከታይ ብዛት፣ በምኞት፣ በስሜት ወይንም በጦር ኃይል ብዛት ወይንም በምድራዊ ገናናነት፣ ስልጣንና ብልጥግና የሚገኝ ነገር አይደለም፡፡ አምላክ ነን ያሉት ሁሉ ተረቶች ሆነው ቀርተዋል፣ ተረስተዋል፡፡ አምላክነትን የሚያሳይ አምላክ የሆነ ብቻ ነው፣ እርሱም በቃላት ቀመር ማረጋገጥ አያስፈልገውም፡፡ አምላክን ከሚሰራው ስራ ያዩ ሁሉ አምላክ መሆኑን ይመሰክራሉ ይህም በግልጥ በጌታ በኢየሱስ ሕይወት ውስጥ ታይቷል፡፡ እርሱ እውነተኛ አምላክ ነውና፡፡

እውነተኛው እግዚአብሔር ከሰራው ስራው በመነሳት ማንነቱን እንዲገነዘቡና አሳቢውን አዕምሯቸውን ተጠቅመው ወደዚህ ድምዳሜ ላይ እንዲመጡ ለራሳቸው ይተዋቸዋል፡፡ ጌታ ኢየሱስንም በወንጌል ውስጥ የምናየው እርሱ እግዚአብሔር የመሆኑን እውነታ ማስረጃ እየሰጠ በሰዎችም እየተመለከ አሁንም እንኳን እየተመለከ ነው፡፡ ይህንን ስንመለከትና ማስረጃውን በትክክል ስናይ በቃላት የተቀመጡ ቀመሮች መኖር አለመኖራቸው አያስጨንቁንም፡፡ በእርግጥም ‹እኔ እግዚአብሔር ነኝ› የሚለውን አረፍተ ነገር የተጠቀመው ሰው፣ ይህንን በመናገሩ ብቻ እርሱ እግዚአብሔር ነው በማለት ልናመልከው አንችልም፣ አረፍተ ነገሩ ብቻውን እርሱ አምላክ ለመሆኑ የሚሰጠው ማስረጃ አይኖርም፡፡ እንዲሁም የምንነጋገርበት ጌታ ኢየሱስ እርሱ እግዚአብሔር ሆኖ እያለና ለእግዚአብሔርነቱ ግልጥ ማስረጃ እያሳየ ‹እኔ እግዚአብሔር ነኝ› የሚለውን ቃል በግልጥ አለመናገሩ የእርሱን እግዚአብሔርነት ሊያስቀረው አይችልም፡፡

የእርሱ እውነተኛ ማንነት የሚታየው ተናግሮ ባደረጋቸው ነገሮች ማለትም በማስረጃዎቹ ላይ ነው፡፡ የጌታ ኢየሱስ አምላክነት አምላክ ሳይሆኑ አምላክ ነን እንዳሉትና የአምላክነት ማስረጃ እንዳላቀረቡት ዓይነት አይደለም፡፡ ነገሮች የሚመዘኑት በንግግር ብቻ ሳይሆን ንግግሮቹን ተከትሎ በታየውና በመጣው ውጤት ጭምር ነውና፡፡

ጌታ ኢየሱስ አምላክ ለመሆኑ ማስረጃውን ከሰጠ በኋላ ሌላ የአረፍተ ነገር መግለጫና ድጋፍ አላስፈለገውም፡፡ ለእውነቱ ልባቸውና አዕምሯቸው ክፍት የሆኑላቸው ሰዎች ማስረጃዎቹን ያያሉ፡፡ ጌታ ላቀረባቸው ማስረጃዎቹ ዝግ የሆኑት፣ በሰዋዊ የሃይማኖተኝነትና የምድራዊ ፍልስፍናም ሐሳብ ታውረው ያሉት በቃላትም ይሁን በሌላ መንገድ ማብራሪያ ቢሰጣቸው ከአለማመናቸው ሊወጡና ወደማመን ሊመጡ አይችሉም፡፡ እናንተም የእርሱን እውነተኛ ማንነት ከተገነዘባችሁ የሚኖራችሁ እውነተኛና ብቸኛ አማራጭ፣ በእግሩ ስር ተደፍታችሁ ንስሐ በመግባት ይቅርታውን ተቀብላችሁ እርሱን በፍጥነት ማምለክ ብቻ ነው፡፡

ጥሪ ለሙስሞች!

ሙስሊም አንባቢዎች ሆይ፣ ጌታ ኢየሱስ ሰው ሆኖ ወደ ምድር የመጣበት ትልቁ ምክንያት በኃጢአት የወደቀውን የሰው ልጅ ለማዳን የሚቻልበት ሌላ ምንም መንገድ ስለሌለ ነው፡፡ እግዚአብሔር ፃድቅ ቅዱስ እና በፍርድ የማያዳላ አምላክ ነው፡፡ እግዚአብሔር ቅዱስና ፃድቅ ስለሆነም በኃጢአት ላይ መፍረድ ይኖርበታል፡፡ የእርሱ ፍርድ ሲገለጥ ደግሞ ኃጢአተኛው ሰው ሊቀበል የሚገባው ነገር የዘላለም የገሃነም እሳት ፍርድ ቅጣትን ብቻ ነው፡፡ ሰውም የሰራው በጎ ነገርና ሃይማኖተኛነቱ ከእግዚአብሔር ፍርድ ሊያድነው አይችልም፡፡

ታዲያ ምን ያስፈልጋል? ሰዎች መዳን ካለባቸው መዳን ያለባቸው ስለ ኃጢአታቸው ቅጣት እና ፍርድ ምትክ ሆኖ የሚከፍልላቸው ካለ ወይንም ከተገኘ ብቻ ነው፡፡ ሌሎች ሰዎች እና የሃይማኖት መሪዎች ይህንን ሊያደርጉ አይችሉም አልቻሉምም፡፡ መላእክትንም ሌሎች ቅዱሳንንም እንኳን ብናስብ አንዳቸውም ሰውን ከዘላለም የገሃም ፍርድ ሊያድኑት አይችሉም፡፡ በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት ያለው ፍፁም ሆኖ መገኘት ብቻ ነው፡፡ ስለዚህም እራሱ ፍፁም የሆነው ጌታ ኢየሱስ ወደ ምድር መጥቶ ለሰዎች ልጆች በደልና ኃጢአት ተሰቃየ፣ የኃጢትንም ሙሉ ዋጋ ከፈለና በመስቀል ላይ ሞተ፣ ይህ ሁሉ የሆነው በእርሱ መስዋዕትነት በኩል ሰዎች ከእግዚአብሔር ጋር ሙሉ ለሙሉ ይታረቁ ዘንድ ነው፡፡

ይህ እውነት በክርስትያኖች የተቀናበረ ወይንም በተለየ ሴራ የተዘጋጀ ሳይሆን፣ ከእራሱ ከእግዚአብሔር ዘንድ የመጣ ነው፡፡ በአጭሩ ያዘጋጀው እግዚአብሔር ነው፡፡ ደግሞም ለትክክለኛ አዕምሮ አስተሳሰብ የሚመች እውነተኛና ሰዎች ሁሉ ሊቀበሉት የሚገባው እውነት ነው፡፡

ኃጢአታችሁ በእግዚአብሔር ዘንድ ይቅር ተብሎ የይቅርታን እውነተኛ ውጤት በሕይወታችሁ ለማየት የምትፈልጉ ከሆነና የዘላለም መጨረሻችሁም የሚያሳስባችሁ ከሆነ፣ አንዱና ብቸኛው መንገድ ወደ ጌታ ኢየሱስ መምጣት ብቻ ነው፡፡ በእርሱ በኩል ታላቅ የዘላለም ሕይወት ምንጭ ተከፍቷል ኑ ወደ እርሱ! ንስሐ ግቡ! እና ኃጢአታችሁን ይቅር እንዲላችሁና የዘላለምን ሕይወት እንዲሰጣችሁ ትርጉም ያለው አዲስ ሕይወት እንዲኖራችሁ እርሱን በትህትና ጠይቁት፡፡

እኛ የእርሱን ስራ በሕይወታችን ውስጥ አይተነዋል፣ ይቅር ብሎናል፣ አዲስን ሕይወት ሰጥቶናል፣ የዘላለምንም ሕይወት ወራሾች አድርጎናል፡፡ አሁን ፀሎታችንና ምኞታችን እናንተም ይህንን እንድትቀምሱትና እንድታዩት ነው፡፡ እኛን የረዳን እግዚአብሔር እናንተንም በፀጋው ይርዳችሁ አሜን፡፡

 

ለእስልምና መልስ አማርኛ  ዋናው ገጽ