የኦሪት ዘዳግም ምርመራዎች

መሐመድ ሐሰተኛ ነቢይ መሆኑን የሚያረጋግጡ፣ ሁለት አጭር፣ ትክክለኛና ቀላል ማስረጃዎች፡፡

David Wood

ትርጉምና ቅንብር በአዘጋጁ

‹ነገር ግን ይናገር ዘንድ ያላዘዝሁትን በስሜ በድፍረት የሚናገር ወይም በሌላ አማልክት ስም የሚናገር ነቢይ፥ እርሱ ይገደል።› ዘዳግም 18.20፡፡

‹በእግዚአብሔር ላይ ነገሮችን ፈጥሬያለሁኝ፣ እንዲሁም ደግሞ እርሱ ያልተናገራቸውን ቃላት ተናግሬያለሁኝ› መሐመድ (አልታባሪ 6.111)፡፡

መሐመድ በቁርአን 7.157 ላይ ‹ለነዚያ ያንን እነሱ ዘንድ በተውራትና በኢንጂል ተጽፎ የሚያገኙትን የማይጽፍና የማያነብ ነቢይ የሆነውን መልእክተኛ የሚከተሉ ለሆኑት (በእርግጥ እጽፋታለሁ) በበጎ ሥራ ያዛቸዋል ከክፉም ነገር ይከለክላቸዋል መልካም ነገሮችንም ለነርሱ ይፈቅድላቸዋል መጥፎ ነገሮችንም በነሱ ላይ እርም ያደርግባቸዋል፡፡ ከነሱም ላይ ሸክማቸውንና እነዚያንም በነሱ ላይ የነበሩትን እንዛዝላዎች (ከባድ ሕግጋቶች) ያነሳላቸዋል እነዚያ በርሱ ያመኑ ያከበሩትም የረዱትም ያንንም ከርሱ ጋር የተወረደውን ብርሃን የተከተሉ እነዚያ እነሱ የሚድኑ ናቸው› እንደተናገረው፣ የአይሁዶችና የክርስትያኖች ቅዱሳን መጻሕፍት የእሱን መምጣት እንደተናገሩ (እንደተነበዩ) ነው፡፡ ይህ አባባል የሙስሊም ዓቃቤ እምነታውያንን ይህንን በተመለከተ የሚናገሩ የብሉይና የአዲስ ኪዳን ክፍሎችን በማበጠር እንዲመረምሩ መርቷቸዋል፡፡ ነቢያቸውን ለማረጋገጥ ሙስሊሞች የሚያቀርቡት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃዎች በጥንቃቄ ሲመረመር የሚያሳየው እነሱ ከሚያቀርቡት በጣም በተቃራኒው ነው (ይህም ሰሚዎቹ ጥቅሶቹን በዓውዳቸው ውስጥ ሲያነቡ ነው)፡፡ ለዚሁም በየጊዜውና በተደጋጋሚ በሚገባ ሁኔታ አጠቃቀሳቸው ትክክል አለመሆኑ ምላሽ ቢሰጠውም አሁንም ሙስሊሞች መጽሐፍ ቅዱስ ስለመሐመድ ይናገራል ሲሉ ይደመጣሉ፡፡

ስለ መሐመድ ይናገራሉ ተብለው ከሚነገሩት በጣም ታዋቂ ትንቢቶች ውስጥ ዘዳግም 18 አንዱ ነው፡፡ በዘዳግም 18 መሠረት መሐመድ በጭራሽ ‹ነቢዩ› አለመሆኑን መማር እጅግ በጣም አስገራሚ የሚሆን ነገር ነው፡፡ እንደምንመለከተውም ይህ እውነታ ሙስሊሞችን በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ያስቀምጣቸዋል፣ እንዲሁም ለነቢያቸው ድጋፍን ለማድረግ በመጣር ምን ያህል እንደሚሄዱ ለማሳየት ይጠቅማል፡፡

የዚህ ጽሑፍም ዓላማ ሙስሊሞች በሚሉት ላይ (ዘዳግም 18 በተመለከተም የሚሉትን ጨምሮ) መሐመድ የሐሰት ነቢይ መሆኑን ማረጋገጥ ነው፡፡ ስለዚህም መሐመድ ነቢይ አለመሆኑን የሚያስረዱ ሁለት ዋና የሆኑ ዓረፍተ ነገሮችን አቀርብና፣ እነሱን በቅደም ተከተል እየተከተልኩኝ ዓረፍተ ነገሮቹን በጥንቃቄ ደግፌ ማስረጃዎቼን አቀርባለሁኝ፡፡ ማስረጃዎቼ የሚያስኬዱና ትክክል መሆናቸውን አንዴ ካቀረብኩኝ በኋላ ደግሞ ከዚህ ውስጥ የሚመጡትን ግልፅ መደምደሚያዎች ለመቃወም ለሚፈልጉ ሙስሊሞች ደግሞ ሊኖር የሚችለውን አማራጭ በመጠኑ እናገራለሁኝ፡፡

አንደኛ፡- የዘዳግም ምርመራዎች

የምርመራ ማስረጃ ሲቀርብ ሁለት ነገሮች ይገኛሉ፣ ተቀባይነት ያለው ሎጂክና እውነተኛ ሐሳቦች ናቸው፡፡ የምርምር ማስረጃ ተቀባይነት አለው ለማለት፣ በሎጂካዊ አቀራረብ መሠረት እውነተኛ ሐሳቦች ሁልጊዜ ወደ እውተኛ መደምደሚያዎች ማምጣት አለባቸው፡፡ በዚህም ውስጥ በጣም መሠረታዊው ማስረጃ ሲሎጂስም ወይንም ከጥቅል ወደ ዝርዝር የሚደረገው የትንተና አካሄድ ነው፣ በጣም ተቀባይነት ያለው ሲሎጂዝም ደግሞ ‹ሞደስ ፖነንስ› የሚባለው ነው (ይህም የአንድን ነገር እርግጠኛነት በማረጋገጫ የሚያረጋግጥ የሎጂክ አካሄድ ነው)፡፡ የሚከተሉት የማስረጃ ሎጂክ መንገዶች ‹የሞደስ ፖነንስ› ናቸው ስለዚህም ሎጂካዊ ተቀባይነት አላቸው፡፡

ማስረጃ አንድ፣ ሀ. ሐሰተኛ አማልክትና ሐሰተኛ ነቢያት

ሀ.1. አንድ ሰው በሐሰተኛ አማልክት ስም ከተናገረ፣ ያ ሰው ሐሰተኛ ነቢይ ነው፡፡

ሀ.2. መሐመድ በሐሰተኛ አማልክት ስም ተናግሯል፡፡

-----------------------------------------------

ሀ.3. ስለዚህም መሐመድ የሐሰት ነቢይ ነበር

 

ማስረጃ ሁለት፣ ለ. ሐሰተኛ መገለጥና ሐሰተኛ ነቢያት

ለ.1. አንድ ሰው ከእግዚአብሔር ያልመጣ መገለጥን ከተናገረ፣ ያ ሰው የሐሰት ነቢይ ነው፡፡

ለ.2. መሐመድ ከእግዚአብሔር ያልመጣ መገለጥን አስተላልፏል

------------------------------------------------

ለ.3. ስለዚህም መሐመድ የሐሰት ነቢይ ነበር

ከዚህ በላይ የቀረቡት የማስረጃዎች ሎጂኮች ሁለቱም ተቀባይነት ያላቸው ስለሆኑ፣ እንዲሁም እውነተኛ ሐሳብ ደግሞ ሁል ጊዜ ወደ እውነተኛ መደምደሚያ ይመራል፡፡ ስለሆነም የእነዚህ መሰረታዊ ሐሳብ እውነት ከሆነ መሐመድ የሐሰት ነቢይ ነበር ማለት ነው፡፡ ስለዚህም አሁን እነዚህን ማስረጃዎቻችንን በጥንቃቄ እንመርምራቸው፡፡

ሁለተኛ፡- ሀ.1. እና ለ.1. ሐሳቦች ተብራርተዋል

ከዚህ በላይ ያሉት ሀ.1. እና ለ.1. ግልጥ ይመስላሉ፡፡ ያም አንድ ሰው በሐሰተኛ አማልክት ስም ከተናገረ ወይንም ከእግዚአብሔር ያልመጡ መገለጦችን ካስተላለፈ ያ ሰው እውነተኛ ነቢይ አለመሆኑ በጣም ግልጥ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በመሐመድ እንዲያምኑ እና እምነታቸውን እንዲቀጥሉ ወደ መጽሐፍ ቅዱስ በማመልከቱ ሙስሊሞች ሁሉ ባለማወቅ ሀ.1. እና ለ.1. እውነት እንደሆነ ተቀብለዋል፡፡

‹ከመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች መከራከር› ለሚለው የእስላሞች አካሄድ መሐመድ እውነተኛ ነቢይ ነበር በማለት በብዙ የሙስሊሞች ትውልድ ዘንድ እንደ መሰረታዊ ማስረጃ ያገለገለው ዘዳግም 18 ነው፡፡ በጣም የታወቀው ‹እስልምናን ለመረዳት አጭር ማብራሪያዊ መመሪያ› የሚባለው ጽሑፍ መጽሐፍ ቅዱስ ስለመሐመድ ይናገራል በማለት ዘዳግም 18 እንደ ዋነኛ መረጃው አድርጎ ይጠቀምበታል፡፡ ስለዚህም I. A. Ibrahim የተባለው የጽሑፉ ጸሐፊ የሚለው ስለመሐመድ መምጣት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትንቢቶች እስልምና እውነት ለመሆኑ ማረጋገጫ ነው በማለት ነው፡፡ ይህም እንደ ማስረጃ የሚጠቀሰው በመጽሐፍ ቅዱስ ለሚያምኑ ሕዝቦች ነው፡፡

በዘዳግም 18 ውስጥ፣ ሙሴ እግዚአብሔር ተናግሮኛል ብሎ የተናገረው ቃል፣ ‹ከወንድሞቻቸው መካከል እንደ አንተ ያለ ነቢይ አስነሣላቸዋለሁ፤ ቃሌንም በአፉ አደርጋለሁ፥ ያዘዝሁትንም ቃል ሁሉ ይነግራቸዋል፤ በስሜም የሚናገረውን ቃሌን የማይሰማውን ሰው እኔ እበቀልለታለሁ።› ዘዳግም 18.18-19፣ ይላል፡፡

መጽሐፉም በመቀጠል የተናገረው መሐመድ ይህንን ትንቢት በብዙ ሁኔታዎች (መንገዶች) እንዳሟላው ነው፡፡ ይህ አባባል ትክክል አለመሆኑ በሚገባ መልስ የተሰጠው ቢሆንም (መሐመድ በመጽሐፍ ቅዱስ የሚለውን ጽሑፍ ተመልከቱ)፣ እዚህ ላይ ግን እኔ በቀላሉ የምጠቅሰው ነገር ሙስሊሞች በዚህ ነጥብ ላይ መጽሐፍ ቅዱስ በእግዚአብሔር መንፈስ የተጻፈ መጽሐፍ መሆኑን መቀበላቸውን ነው፡ (ምክንያቱም እነሱ ይህንን ጥቅስ እንደ ተዓምራዊ ትንቢት ስለሚቆጥሩት ነው)፡፡ በእርግጥ ታዲያ የሚቀጥለውን ጥቅስ ልንዘነጋው ግን አንችልም፣ ይህም እግዚአብሔር እንደሚከተለው የተናገረበትን ነው፣ ‹ነገር ግን ይናገር ዘንድ ያላዘዝሁትን በስሜ በድፍረት የሚናገር ወይም በሌላ አማልክት ስም የሚናገር ነቢይ፥ እርሱ ይገደል።› ዘዳግም 18.20፡፡

እንግዲህ እዚህ ላይ እኛ የሐሰተኛ ነቢይን ለመለየት የሚያስችሉ ሁለት መስፈርቶች አሉልን እነዚህም፡- 1. እግዚአብሔር ተናገረ ብሎ ያልተናገረውን መልክት ማስተላለፍ፣ እንዲሁም 2. በሌሎች ነቢያት ስም መናገር የሚሉት ናቸው፡፡ ሙስሊሞች ይህንን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትንቢት የሚሉትን ጥቅስ ለመሐመድ ነቢይነት ማረጋገጫ ማህተም አድርገው ስለሚሰጡት እነሱ አሁን ከዚህ በላይ የቀረቡትን የሐሳብ ነጥቦች ማለትም ሀ.1. እና ለ.1. ሊክዱ አይችሉም፡፡ ነገሩን ለማጠቃለልም ሙስሊሞች በዘዳግም 18 ላይ ያለውን ክፍል ይጠቅሳሉ ይህም ሀ.1. እና ለ.1. ላይ ያሉትን ሐሳቦች ያመለክታል፡፡ ስለዚህም እንደሙስሊሞች አባባል ከሆነ የመጀመሪያው ሐሳብ በዘዳግም 18 ትንተና መሠረት ትክክል ነው፡፡

ሦስተኛ፡- ሀ.2. እና ለ.2. ተብራርተዋል

በብዙ ሙስሊሞች የመለኮታዊ መገለጥ ነው ተብሎ በተነገረው አንቀፅ መሠረት የተመለከትነው ከእግዚአብሔር ያልመጣውን መልእክት ያስተላለፈ ሰው ወይንም በሌሎች አማልክት ስም መልእክትን ያስተላለፈው ሰው መሆን ያለበት ሐሰተኛ ነቢይ ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ማለት መሐመድ ሐሰተኛ ነቢይ ነበር ነው ምክንያቱም እርሱ ሁለቱንም አድርጓልና ይህም እጅግ የታወቀውን ሰይጣናዊ ጥቅሶችን ሲያስተላልፍ ነበር፡፡

ስለነዚህ ሰይጣናዊ ጥቅሶች የምንማረው ከክርስትያን ወይንም ከአይሁዶች ከመጡ ምንጮች ውስጥ አይደለም፣ ነገር ግን ከጥንት የሙስሊም ጽሑፎች ውስጥ ነው፡፡ የሰይጣናዊ ጥቅሶች ዘገባዎች በብዙ የጥንት ምንጮች ውስጥ ተዘግበው ይገኛሉ እነዚህም የሚጨምሩት፡- 1. ኢብን ኢሻክ፣ 2. ዋኪዲ፣ 3. ኢብ ሳኣድ፣ 4. አል-ታባሪ፣ 5. ኢብን አቢ ሐቲም፣ 6. ኢብን አል-ሙንዲር 7. ኢብን ማርዱህ፣ 8. ሙሳ ኢብን ኡቁባ እና 9. አቡ ማሻር ናቸው፡፡ (መሐመድና ሰይጣናዊ ጥቅሶች የሚለውን ጽሑፍ ይመልከቱ)፡፡ በሙስሊሞች ታላቅ ሊቅ ኢብን ሃጃር መሠረት በሦስት ተከታታይ ‹ኢስናዶች› መሠረት ዘገባዎቹ፡- ‹ለእርግጠኛ ዘገባ የሚያስፈልጉትን ሁኔታዎች ያማላሉ›፡፡ በተጨማሪም ደግሞ Sahih al-Bukhari በመሐመድ ሕይወት ላይ በጣም ታማኝ የሆነው የእስልምና ምንጭ ስለ ክስተቱ ቀጥተኛ ያልሆነ ማረጋገጫን ይሰጠናል (ቁጥር 4862 ከዚህ በታች ተጠቅሷል)፡፡ ከዚህም በላይ የቁርአን ጥቅሶች 17.73-75 እና 22.52-53 የተገለጡት መሐመድ ወደ አሳፋሪ የብዙ ጣዖት አምልኮ (ፖሊቲዝም) ውስጥ በማዘንበሉ ጭምር ነበር፡፡

ስለዚህም እኛ ታሪኩ ትክክል ለመሆኑ እጅግ በጣም አሳማኝ የሆኑ ታሪካዊ ማስረጃዎች አሉን፡፡ (ጥልቅ ለሆነው የሰይጣናዊ ጥቅሶች ማስረጃ ‹መሐመድና ሰይጣናዊ ጥቅሶች› የሚለውን ተመልከቱ፡)፡፡ በእርግጥ የታሪካዊው ዘዴ በትክክል የታሪኩን ታማኝነት ያረጋግጣል፡፡ የመሪዎችን እና የሃይማኖት ታላላቅ ሰዎችን ሕይወት የሚመረምሩ የታሪክ ተመራማሪዎች የሚጠቀሙበት "Principle of Embarrassment," ‹የሐፍረት መርሆ› የሚባል ስነ ዘዴ አላቸው፡፡ ይህም ስነ ዘዴ ሕጋዊ ምርመራዎች ላይ ከፍተኛ ትኩረትን ይሰጣል፡፡ የሕግ ፕሮፌሰር Annette Gordon-Reed መርሆውን እንደሚከተለው አጠቃለውታል ‹ፀረ የግል ጥቅም መግለጫዎች እንደ አንድ ከፍተኛ ደረጃ ታማኝነት ያለው ማስረጃ ይቆጠራሉ፣ ምክንያቱም ሰዎች እራሳቸውን ለመጉዳት ሲሉ ውሸትን እንደማይዋሹ ስለሚገመት ነው፣ የሚዋሹት እራሳቸውን ለመርዳት ነውና› Annette Gordon-Reed, Thomas Jefferson and Sally Hemings: An American Controversy (Charlottesville: University of Virginia Press, 1997). የሐፍረትን መርሆ በሰይጣናዊ ጥቅሶች ዘገባ ላይ ስናውለው ወዲያውኑ የምንመለከተው ሙስሊሞች ይህንን ታሪክ እራሳቸው እንዳልፈጠሩት ነው፣ ምክንያቱም ይህ የመሐመድን ታማኝነት ጥያቄ ውስጥ የሚጥለው ነውና፡፡ እንደዚሁም የምንመለከተው ታሪኩ ሙስሊሞች ባልሆኑት ሰዎች የተፈጠረም እንዳልሆነ ነው ምክንያቱም ሙስሊሞች ያልሆኑ ሰዎች ይህንን ታሪክ ፈጥረውት ቢሆን ኖሮ፣ ሙስሊሞች ከጥንታዊ ምንጮቻቸው ጀምሮ ከሚከራከሩለት ይልቅ የታሪኩን ምንጭ ያጋልጡት ነበርና ነው፡፡

ስለ ሰይጣናዊ ጥቅሶች ታማኝነት ያለው የሙስሊሞች መረጃ እጅግ በጣም ብዙ ነው ስለዚህም ከብዛቱ የተነሳ ይህንን ሁሉ ማስረጃ ለመዝጋት በፍፁም አይቻልም፡፡ ይህን በአዕምሮአችን እንደያዝን በአል-ታባሪ የተጨመቀ ታሪክ ውስጥ ያለውን እንደሚከተለው እንመለክት፡፡

በአል ታባሪ መሠረት

የእግዚአብሔር መልእክተኛ የራሱ ነገዶች በእርሱ ላይ ጀርባቸውን እንዴት እንዳዞሩ (እና መልእክቱን እንዳልተቀበሉ) ባየ ጊዜ በጣም አዘነ ምክንያቱም ለእነሱ ከእግዚአብሔር ያመጣውን መልእክት በመዝጋታቸው ነበር፡፡ ከዚያም እሱ በነፍሱ ውስጥ ከእግዚአብሔር ዘንድ አንድ ነገር መጥቶ ከእነሱ ጋር መታረቅ የሚችልበትን ነገር ናፈቀ፡፡ ለጎሳው ካለው ፍቅርና ለእነሱም እሱን ደስ የሚያሰኘው መልካምን ነገር እንዲሆንላቸው፣ በእሱ ላይ ያመጡት አንዳንዶቹ ችግሮች እንዲቃለሉም ነበር፡፡ ከዚያም እርሱ በውስጡ፣ ማለትም ከራሱ ጋር ይከራከር ነበር እናም እንዲህ ዓይነት ነገር እንዲመጣ በጣም ይፈልግ ነበር፡፡ ከዚያም እግዚአብሔር የሚከተለውን ገለጠ፡-

‹በኮከብ እምላለሁ በወደቀ (በገባ) ጊዜ፡፡ ነቢያችሁ አልተሳሳተም አልጠመመምም ከልብ ወለድም አይናገርም ...› እናም ወደ እነዚህ ቃሎች በመጣ ጊዜም ‹አል-ላትንና አል-ዑዛን እንዲሁም መናትን አያችሁን?› ሰይጣን በምላሱ ላይ እነዚህን ቃላት አስቀመጠ፣ ይህም በውስጡ በነበረው ክርክር የተነሳ እና ጎሳዎቹን (ወደ እምነቱ) ለማምጣት ከነበረው ከፍተኛ ፍላጎት የተነሳ ነበር፣

እነዚህ ቃላት ከፍ ብለው የሚበርሩ ዓይነት ዕቃ ማንሻዎች ነበሩ፣ በእርግጥም የእነሱ ምልጃ በማረጋገጫ ተቀባይነትን አግኝተው ነበር (Al-Tabari, p. 108)፡፡

እነሱም መሐመድ በስተመጨረሻው ላይ የእነሱን አማልክት ስለተቀበላቸው ብዙዎቹ ጣዖት አምላኪዎች ተደስተው ነበር፡፡ ለዚህም አድራጎቱ ምላሽን ለመስጠት ‹(ከእርሱ ሲነገር) ለሰሙት የአማልክቶቻቸው ስም መጠቀስ ሰገዱ ስለዚህም በመስጊዱ ውስጥ በአማኝም ይሁን ባላመነ ሰው መካከል ያልሰገደ አንድም ሰው አልነበረም› (Al-Tabari, p. 109}፡፡

መሐመድ ከጣዖት አምላኪዎቹ ጋር የነበረው ወዳጅነት ግን የቆየው ለጥቂት ጊዜ ብቻ ነበር፣ ይሁን እንጂ እርሱ ወዲያውኑ የተረዳው ነገር የፓጋን ጣዖታትን የሚያመስግኑት እነዚህ ቃላት ከእግዚአብሔር ያልመጡ መሆናቸውን ነገር ግን ከሰይጣን የመጡ መሆናቸውን ነበር፡፡ አላህንም በማታለሉ በጣም አዘነ፣ መሐመድም እጅግ አዝኖ እንደዚህ አለ፡ ‹በእግዚአብሔር ላይ እኔ ነገሮችን ፈጥሬያለሁ እንዲሁም እሱ ያልተናገረውን ነገር በእሱ ላይ አድርጌበታለሁኝ አለ› (Al-Tabari, p. 111)፡፡ ነገር ግን ገብርኤል እርሱን አፅናናው እንዲህም አለው ከእርሱ በፊት የመጡት ነቢያት በሙሉ ከጊዜ ወደ ጊዜ በሰይጣን ዘዴ ውስጥ እንደወደቁ ነገረው፡፡ ይህ አስደናቂ እንዲሁም ሊታመን የማይቻል አባባል በቁርአንም ውስጥ እንኳን ተቀምጦ ይገኛል፡- 

‹ከመልክተኛና ከነቢይም ከአንተ በፊት አንድንም አልላክንም ባነበበ(ና ዝም ባለ) ጊዜ ሰይጣን በንባቡ ላይ (ማጥመሚያን ቃል) የሚጥል ቢኾን እንጂ ወዲያውም አላህ ሰይጣን የሚጥለውን ያስወግዳል ከዚያም አላህ አንቀፆቹን ያጠነክራል አላህም ዐዋቂ ጥበበኛም ነው፡፡› ቁርአን 22.52፡፡ ከዚህም ጥቅስ ቀጥሎ ባለው ጥቅስ ውስጥ ነቢያቶቹ ከሰይጣን ጥቅስን እንዲቀበሉ አላህ እንደሚፈቅድ ይናገራል ይህም ልባቸው ጠንካራ የሆኑትን ሰዎች ለመፈተን ነው ይላል፡፡

የሰይጣናዊ ጥቅሶችን በተመለከተ የማይረባ ምንም ዓይነት የቁርአን ገለጣን ለማምጣት እናስብ (እና መሐመድ ያቀረበውንም መከላከለያ ጭምር)፡፡ ይሁን እንጂ በጣም ግልፅ የሆነው ነገር የእስላም ነቢይ ቢያንስ በአንድ ወቅት ከእግዚአብሔር ያልመጣ መልእክትን አስተላልፏል የሚለው ነው፡፡ እንዲሁም ደግሞ መሐመድ ቢያንስ በአንድ ቦታ ላይ በሌሎች አማልክት ስም መልእክትን ተናግሯል የሚለው ነው፡፡ ስለዚህም እኛ አሁን ከሙስሊሞች ምንጮች በመነሳት ሀ.2. እና ለ.2. በእርግጠኝነት እውነት እንደሆኑ ማረጋገጥ እንችላለን፡፡

አራተኛ፡- ሊሆኑ የሚችሉ ምላሾች

ከላይ የሰፈሩትን ሀ.1.፣ ሀ.2.፣ ለ.1. እና ለ.2. ለመቀበል ጥሩ ምክንያቶች ስላሉን ሀ.3. እና ለ.3. ላይ ያሉት መደምደሚያዎችንንም እንደዚሁ ለመቀበል የሚያስችሉን ምክንያቶች አሉን፡፡ ሁለቱም የሚናገሩት መሐመድ የሐሰት ነቢይ መሆኑን ነው፡፡  ይሁን እንጂ ይህንን መደምመዲያ ሙስሊሞች ለመቀበል አይፈልጉም፡፡ እነሱ ይህንን ላለመቀበል የሚያቀርቡትን ነገር በመጠኑ እንመልከት፡፡

በእርግጥ ዘዳግም 18.20 በእግዚአብሔር ያልተሰጠ የሐሰት ትምህርት ነው ለማለት ሙስሊሞች ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ይህንን መንገድ የሚወስዱ ከሆነ ደግሞ ዘዳግም 18.18-19 በእግዚአብሔር የተሰጠ ትንቢት ነው ወደማለት ቢመለሱ ይህ ለእነሱ የሚሆነው እጅግ በጣም ተራ ነገር ነው፡፡ በሙስሊሞች መካከል የመጽሐፍ ቅዱስን ክፍል አንዱን መርጦ አንዱን መጣል እጅግ በጣም አስደንጋጭ በሆነ መልኩ የተለመደ ቢሆንም እንኳን (ማለትም ከእስልምና ጋር የሚስማማው ማንኛውም ነገር ትክክል ነው ነገር ግን ከእስልምና ጋር የማይስማማው ነገር ሁሉ ስህተት ነው እናም በክርስትያኖችና በአይሁዶች የተበከለ ነው የሚሉት አባባል)፣ በሚከተሉት አካሄድ ማንም ሰው ሊስማማም ሊያምንም አይችልም፣ ምክንያቱም በዘዳግም 18 ላይ አንድ ጥቅስ የመሐመድን ነቢይነት የሚያረጋግጥ ሲሆን ሌላው ጥቅስ ከዚያ ቀጥሎ ያለው ደግሞ የተበከለ ነው ምክንያቱም የእሱን የሐሰት ነቢይነት ስለሚያረጋግጥ ማለት አይቻልምና፡፡

ስለሆነም ሀ.1. እና ለ.1. ለመካድ የሚፈልጉ ሙስሊሞች ዘዳግም 18 የመሐመድን ነቢይ ሆኖ መምጣት ይናገራል ብለው የሚሉትን መተው ይኖርባቸዋል፡፡ በዚህ አቀራረብ ለሙስሊሞች የሚያመጣው ከፍተኛ ችግር ነው፡፡ እንደ ሙሴ ያለ ነቢይ የመምጣቱ ትንቢት በመጥቀስ ሙስሊሞች ሊያነሱት ወይንም ሊጠቀሙበት የሚችሉት የመጨረሻ ጥቅስ ዘዳግም 18 ብቻ በመሆኑ ነው፡፡ ይህንንም የሚያደርጉት ትክክል አለመሆኑን ማለትም ተቀባይነት ሊኖረው እንደማይችል ከሚያስረዱት ጭብጥ ማስረጃዎች ውጪ በመሄድ (ማስረጃዎቹን በመዝጋትም) ጭምር ነው፡፡ ይህም መሐመድ እንደነቢይ ተቀባይነት ያገኝልናል በሚል ባዶ ተስፋ ላይ በመንጠልጠል ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ ግልፅ የሆነን ትንቢት ስለመሐመድ ካልያዘ (ከሌለው) መሐመድ አሁንም ሊሆን የሚችለው የሐሰት ነቢይ ነው፡፡ እሱ የአይሁድና የክርስትያኖች መጽሐፍቶች ስለ እሱ መምጣት ትንቢትን ይናገራሉ ብሎ በቁርአን ውስጥ በመናገሩና ከነዚያም ያላነሰ መሆኑን በመናገሩ ነው፡፡ ይህም የሚያስረዳው ሙስሊሞች የተቀመጡት በመምታታት ቀንበር ስር ነው ማለት ነው፡፡ ስለዚህም ሙስሊሞች አሁንም በዘዳግም 18 ላይ የሚንጠለጠሉ ከሆነ መሐመድ በትክክል የሐሰት ነቢይ ነው ማለት ነው፡፡ ይህንን ደግሞ ከተውት የሚሆነውና ሊሆን የሚችለው ደግሞ እነሱ ስለነቢያቸው የተነገረ ያለምንም የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ይቀራሉ ማለት ነው፣ ይህም ደግሞ የሚያሳየው መሐመድ አሁንም የሐሰት ነቢይ የነበረ መሆኑን ነው፡፡

ይሁን እንጂ ሙስሊሞች እጅግ በጣም የሚያከብሩትን ትንቢት የጣሉትና የተውት ሙስሊሞች አሁንም እዚያው ውስጥ ናቸው (ከዚያው ውስጥ አልወጡም)፡፡ ዘዳግም 18 ቢተውትም እንኳንና ሙሉ ለሙሉ የተበከለ ነው ቢሉም እንኳን ይህ ከዚህ በላይ ያስቀመጥናቸውን ሀ.1. እና ለ.1. ሊያፈርሳቸው አይችልም እኔ ከዚህ በፊት እንደተናገርኩት ሁሉ እነዚህ ሐሳቦች እጅግ በጣም ግልጥ ናቸውና፡፡ ሀ.1. እና ለ.1. ለመካድ የሚፈልጉ ሙስሊሞች ማሳየት የሚኖርባቸው ነገር እነዚህ ሐሳቦች ስህተት ናቸው ምክንያቱም እውነተኛ ነቢይ የሐሰት ትንቢትን ሊያስተላልፍ ይችላል እንዲሁም በሐሰት አማልክት ስም ሊናገር ይችላል የሚለውን ነገር ነው፡፡  ሙስሊሞች እንዲህ ዓይነት ሊደረግ የማይቻልን አቋም ሲናገሩ መስማትንና ማየትን በጣም እፈልጋለሁኝ፡፡      

ስለዚህም የሚመስለው በመሐመድ ነቢይነት ማመናቸውን ለመቀጠል አሁንም የሚፈልጉ ሙስሊሞች ሀ.1. እና ለ.1. መካድ እንደሌለባቸው ነው ነገር ግን ሀ.2. እና ለ.2 እንደሚክዱ ነው፡፡ ነገር ግን ይህ የሚሆነው ደግሞ እጅግ በጣም ብዙ ታሪካዊ እንዲሁም ቁርአናዊ ማስረጃ ያለውንና መሐመድ ለጊዜውም ቢሆን የፓጋን አማልክትን ደግፎ የተናገረባቸውን ማስረጃዎችን ሁሉ መካዳቸው ነው፡፡ ይህን አካሄድ የሚከተሉ ሙስሊሞች የሚከተሉትን ሰባት ነገሮች የግድ ማድረግ ይኖርባቸዋል እነዚህም፡-

አንደኛ፡- ለታሪኩ ጅማሬ የሚሆን አጥጋቢ ገለፃን መስጠት ይኖርባቸዋል (ለምሳሌም ታሪኩ በፓጋኖች በክርስትያኖች ወይንም በአይሁዶች ለመፈጠሩ አሳማኝ ነገርን ማቅረብ ይኖርባቸዋል)፡፡

ሁለተኛ፡- እንደዚህ ዓይነትን ታሪክ ላለመቀበል ማንኛውም አጋጣሚ የነበራቸው ሙስሊሞች እውነት እንደሆነ ተቀብለው ለምን እንዳስተላለፉት ማብራሪያን መስጠት ይኖርባቸዋል (ከሌሎች የተፈጠረ ፈጠራ ነው ከማለት ይልቅ)፡፡

ሦስተኛ፡- ኢብን ኢሻክ፣ ዋኪዲ፣ ኢብ ሳኣድ፣ አል-ታባሪ፣ ኢብን አቢ ሐቲም፣ ኢብን አል-ሙንዲር፣ ኢብን ማርዱህ፣ ሙሳ ኢብን ኡቁባ እና አቡ ማሻር የሚባሉት የሙስሊም ታሪክ ጸሐፊዎች አሳሳች ታሪክ ጸሐፊዎች መሆናቸውን ማሳየት ይኖርባቸዋል (በጣም የሚያስገርም ስህተት ነውና እነሱ ይህንን ስለ መሐመድ የሚናገረውንና ነቢይነቱን እንድንጠይቅ የሚያደርገውን የውሸት ታሪክ ጨመሩበት)፡፡

አራተኛ፡- ለሚያቀርቡት ነገር እርግጠኛነት ለማስረዳት የመጀመሪያዎቹ የሙስሊም የግል ሕይወት ታሪክ ጸሐፊዎች ለሚጠቅሷቸው እጅግ በጣም ብዙ የሆኑ ምንጮችን መጥቀስ (መመልከት) ይኖርባቸዋል፡፡  

አምስተኛ፡- አል-ቡካሪ፣ የእስላም በጣም ታማኝ የሆነው ጸሐፊ፣ መሐመድ በእርግጥ የሰይጣን ጥቅሶችን አስተላልፎ ከሆነ ብቻ ትርጉም የሚሰጡትን ጥቃቅን ዝርዝሮችን የሰጠውን ሰው ይህንን ለምን እንዳደረገው ማስረዳት ይኖርባቸዋል፡፡ በአል-ቡካሪ መሠረት የሚከተለውን እናገኛለን፡- ነቢዩ ሱረቱ 53 ከጨረሰ በኋላ ነቢዩ ሰገደ ሙስሊሞችም በሙሉ ሰገዱ፣ እንዲሁም (ብዙ አማልክትን የሚያመልኩት፣ ጣዖት አምላኪዎቹ፣ እና በአላህ አንድነትና በነቢዩ በመሐመድ የማያምኑትም ሁሉ፣ ሁሉም ሰገዱ ከእሱም ጋር ጂኒዎችና የሰዎች ልጆችም ሁሉ አብረው ሰገዱ፡፡) Sahih Al-Bukhari, Volume Six, Muhammad Muhsin Khan, tr. (Riyadh: Darussalam, 1997 4862)፡፡

ምንም እንኳን አል-ቡካሪ ፓጋኖቹ ለስግደቱ ምክንያት የሆናቸውን አሳፋሪ ነገር ሆነ ብሎ ቢዘልለውም፣ የኢብን-ኢሻክንና የሌሎችንም ዘገባዎች፣ ማለትም በእውነት ፓጋኖቹ የሰገዱት መሐመድ የእነሱን ጣዖታት በተመለከተ መልካምን ነገር ስለተናገረ መሆኑን በታማኝነት የጠቀሱትን ግን ባለማወቅ አረጋግጦታል፡፡

ስድስተኛ፡- ሙስሊሞች ለቁርአን 22.52 ተጠያቂዎች መሆን አለባቸው፣ ይህም ጥቅስ እንደገና የሚያውጀው ሁሉም የእግዚአብሔር ነቢያት ከሰይጣን መገለጥን ሊያገኙ እንደሚችሉ የሚናገረውን ነው - ይህ ጥቅስም በጣም ተራ የሆነ ሲሆን እንዲህ ዓይነቱ ነገር ሊሰጥ የሚችለው እንደ ሰይጣናዊ ጥቅሶች ያሉ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ፣ ለሙስሊም ማኅበረሰብ የሚሰጥ መግለጫ ብቻ ነውና፡፡

ሰባተኛ፡- ሙስሊም ላልሆኑት ሁሉ እንደዚህ ዓይነት ብዙ ተጨባጭ ማስረጃዎችን ለምን እንደማይቀበሉና መሐመድን ታማኝ ነቢይ አድርገው እንደተቀበሉ ማሳየት አለባቸው፣ ይህም የተነገራቸው ሙስሊሞች ሁሉ ሲቀበሉ፣ መሐመድ የጥቁር አስማት ቁጥጥር ስር እንደበረ (በአይሁድ አስማተኞች አስማት ተደርጎበት)፤ እንዲሁም በአንድ ነጥብ ላይ እርሱ እራሱ በአጋንንት የተያዘ መሆኑን አምኖ እያለ ነው፡፡ በሌላ መልኩ አስቀምጡት፣ የእስላም ነቢይ በአጋንንት መያዙን በስህተት አምኖ ቢሆን ኖሮ፣ እናም ለመንፈሳዊ ጥቃት የተጋለጠ የነበረ ከሆነ (እንደ ጥቁር አስማት) ከሰይጣን መልእክትን አልተቀበለም በማለት ለማመን የምንገደደው ለምንድነው? (ለተጨማሪ ማስረጃ ‹አስማት የተደረገበት ነቢይ› የሚለውን ጽሑፍ ያንብቡ)፡፡

ለሰይጣናዊ ጥቅሶች ያሉትን ታሪካዊ ማስረጃዎችን ሙስሊሞች ለማስወገድ እንደሚሞክሩ እኔ እየመሰከርኩኝ፣ ነገር ግን ማስረጃዎቹን ለማስወገድ የሚጠቅሙ በሩቁ እንኳን ሊደግፉ የሚችሉ ምንም አሳማኝ ነገሮችና ማግኘት አልቻልኩኝም፡፡ ለምሳሌም ያህል በመሐመድ ነቢይነት ጥያቄ ላይ ባደረግሁት ክርክር በ U. C Davis, ተከራካሪዬ የነበረው አሊ አታይ የሞከረው፣ ሰይጣናዊ ጥቅሶችን በተመለከተ አል-ቡካሪን የሰጠውን የተዘዋዋሪ ማስረጃን በተመለከተ ለመመለስ ነበር፡፡ በዚህም የሞከረው የቁርአንን ተዓምራታዊ ኃይል ለማሳየት ነበር፡፡ በአታይ መሰረት ፓጋኖች የሰገዱት ቁርአን 53 በማክበር እንደነበረ ነው (ይህም አሁን ባለበት ሁኔታ ፖሊቲዝምን የሚያቃልል ተደርጎ በቀረበበት ሁኔታ ማለት ነው) በግርማዊነቱ በጣም እጅግ ተገርመው ማለት ነበር፡፡ ነገር ግን እንዲዚህ ዓይነት ምላሾች የተመሠረቱት በቅዠት ላይ እንጂ በእውነታ ላይ አይደለም፡፡ ሙስሊሞች ለሺ ዓመታት ቁርአንን በቃል ሲያነበንቡት ኖረዋል፣ በእስልምና የማያምኑቱ ደግሞ በተለይም በመሐመድ ግጥም ምንም አልተማረኩበትም፡፡ በእርግጥ መሐመድ ቁርአንን ለመለኮታዊ መልክተኛነቱ ማስረጃ እንዲሆን ሲናገር በጣም ጥቂት ሰዎችን ተከታዮቹ እንዲሆኑ አድርጓል ፡፡ ነገር ግን ብዙ ተከታዮችን ሊያገኝ የቻለው ወደ ሌላው ጎን ሲመለስ ነበር (በደም ማፍሰስ ነበር) ሰዎችን የመለወጥ መንገድ፡፡ ስለሆነም እንደ አታይ ላሉ ሙስሊሞች፣ ፓጋኖች በአንድ ላይ ሆነው ቁርአን 53ን መሐመድ ሲያስታውስ አብረው ሰገዱ ብሎ ማለት በተምታታ ድንበር ላይ መቆም ብቻ ነው የሚሆነው፡፡ የቡካሪ ሐዲት በእነ ኢብ ኢሻክ የታሪካዊ ስራ ዓይን ሲታይ የበለጠ ትርጉምና ስሜት ሰጪ ነው የሚሆነው (ይህም ከሳሂህ አል-ቡካሪ በብዙ አስርተ ዓመታት ቀድመው የተጻፉ ናቸውና)፡፡ ቁርአን 53 ሲነገር ፓጋኖች በአክብሮት የሰገዱበት አሳማኙ ብቸኛ ምክንያት የሚሆነው ሱረቱ 53 በመጀመሪያው አነጋገሩ ፓጋኒዝምን (የብዙ ጣዖት አምልኮን) ስለ ደገፈ ብቻ ነው፣ ይህም የጥንቶቹ እስላማዊ ታሪካዊ ማስረጃዎቻችን ሁሉ የሚደግፉት እውነታ ነው፡፡

ከዚህ በላይ ያሉት ሁሉም ነገሮች በአንድ ላይ ሲታዩ የምንመጣበት ብቸኛ መደምደሚያ የሚሆነው፣ ከታሪካዊው ማስረጃዎች ላይ እንደሚከተለው ነው ‹መሐመድ በድካሙ ወቅት በፈተና ውስጥ ወደቀና በከፍተኛ ደረጃ ፖሊቲዝምን ደገፈ ይህንንም ያደረገው ከሰይጣን መገለጦችን አምጥቶ ነበር የሚለው ነው›፡፡ ነገር ግን ይህ ደግሞ እኛ በእርግጥ በማስተዋል ውስጥ ከሆነን ሀ.2. እና ለ.2. ልንክድ አንችልም ማለት ነው፡፡ ስለዚህም ሙስሊሞች ለዘዳግም ማስረጃ ምንም ዓይነት ጥሩ ምላሽን ሊሰጡ አይችሉም ማለት ነው፡፡ በመሆኑም እኛ የሚቀረን ነገር ቢኖር ልንርቀው የማንችለው መደምደሚያ ነው የሚሆነው እርሱም መሐመድ የሐሰት ነቢይ ነበር ማለት ነው፡፡

አምስተኛ፡- ግምገማ

ለማጠቃለል ያህል እኔ እንደገና ትኩረት ልሰጥበት የምፈልገው ነገር የኔ አጠቃላይ ሐሳብ (በሁለቱ ማስረጃዎች መሰረት) የተመሰረተው በሙስሊሞች ጽሑፎችና በሚናገሩት ላይ ነው፡፡ የቀደሙት የሙስሊሞች ታሪክ ጸሐፊዎች በሚያስደንቅ የእውነተኝነት ሐቀኛ ማስረጃ ያቀረቡት ነገር ነቢያቸው ሰይጣናዊ ጥቅሶችን ለሰሚዎቹ እንዳስተላለፈ ነው፡፡ ይህንንም በማመን ለ(ሀ.2.) እና ለ(ለ.2.)  የሚያስፈልጉትን ማስረጃዎች ሁሉ ሰጥተውናል፡፡ ዘመናዊ ሙስሊሞች መሐመድ አገልግሎቱ ተቀባይነት እንዲኖረው መጽሐፍ ቅዱሳዊ እንደሆነ መናገሩን ለመሸፈን ሲሉ የዘዳግም 18 ቃል በእግዚአብሔር የተሰጠ መለኮታዊ ጽሑፍ ነው ብለውልናል፡፡ ይህንንም በማድረጋቸው ለ(ሀ.1.) እና ለ(ለ.1.) መሰረታዊ ሐሳቦች የሚያስፈልጉትን ነገሮች ሁሉ ሰጥተውናል፡፡ የዘዳግም 18 ማስረጃዎች ሎጂካዊ ተቀባይነት ያላቸው ስለሆነ እኛ ሁለት ማስረጃዎች አሉን እነዚህም በሙሉ በሙስሊሞች አባባል ላይ ሙሉ በሙሉ የተመሰረቱ ናቸው፣ ማለትም መሐመድ የሐሰት ነቢይ ነበር ማለት ነው፡፡

የዘዳግም ማስረጃ ትክክለኛ ስለሆነ (ስለሚያስኬድ) (ማለትም ሎጂካዊ ተቀባይነት ስላለው በእውነተኛ ሐሳብ ላይ ተመስርቶ) ማንኛውም እውነተኛ የሆነ እውነትን ፈላጊ መቀበል የሚኖርበት መሐመድ የሐሰት ነቢይ የነበረ መሆኑን ነው፡፡ ስለዚህም ይህ እውነታ እውነትን የሚያሳይ ነገር ነው የሚሆነው፣ ይህም ይህንን እውነታ ለሙስሊሞች ማቅረብ ግሩም እርዳታ ማድረግ ነው፡፡ አንድ ሙስሊም ይህንን አቀራረብ በጥንቃቄ ቢመረምረው ሐሳቦቹን ቢያስተውልና ማስረጃዎቹንም ቢመዝን፣ ከዚያም በኋላ መደምደሚያዎቹን የሚያፈርስበትን ማስረጃ ሳያቀርብ እንደዚሁ አልቀበልም ቢል፣ እኛ ለእንደዚህ ዓይነቱ ሰው አቀራረብ ልንገምት የምንችለው ነገር ቢኖር እንዲህ ዓይነቱ ሰው ለእውነት ደንታ የሌለው፣ እና በጣምም ዝንባሌ ያለው ያደገበትን እምነት በጭፍን በመቀበል ለመጽናናት በመጣጣር ላይ ብቻ ነው በማለት ነው፡፡ ምንም እንኳን እስከ አሁን ያየሁት ልማዴና ያገጠመኝ ነገር የመራኝ ብዙዎቹ ሙስሊሞች እንደዚህ ዓይነቶች እንደሆኑ እንዳምን ቢሆንም፣ የኔ ልምድ ገጠመኝ ሌላው ጎን ደግሞ ያሳየኝም በዓለም ውስጥ ስለ እግዚአብሔር እውነቱን ለማወቅ በጣም በትጋት የሚጣጣሩ ሙስሊሞች እንዳሉም ጭምር ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነቶቹ ሙስሊሞች ሊማሩት የሚገባቸው የመጀመሪያው እውነት የእነሱ ነቢይ በምንም ዓይነት መንገድ ቢሆን ነቢይ እንዳልነበረ ነው፡፡ ሁለተኛው እውነት ደግሞ እነሱ ነቢይ ነው የሚሉት ኢየሱስ ደግሞ ከነቢይ እጅግ በጣም የበለጠ እንደሆነ ነው፡፡ (ነገር ግን ይህንን ለሌላ ጽሑፍ እተወዋለሁኝ)፡፡

የአዘጋጁ ማሳሰቢያ፡-

ከዚህ በላይ ያየነው ኦሪት ዘዳግም ላይ የተመሰረተው ጽሑፍ አስገራሚ እውነታን ይፈነጥቃል፡፡ መሐመድ እውነተኛ ነቢይ ካልሆነና በማስረጃ እንዲህ ከተረጋገጠ እራሳችንን መጠየቅ የሚገቡን ብዙ ጥያቄዎች ሊኖሩ ይገባል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ መሐመድ ስለ ክርስቶስ የተናገራቸው ነገሮችም ይገኙበታል፡፡ መሐመድ ስለ ክርስቶስ እውነትን ተናግሯልን? እሱ እውነትን ካልተናገረና የክርስትያኖች እምነት እውነት ከሆነስ? መጨረሻችን ኪሳራና ለዘላለም አሳዛኝ አይሆንምን? በተለይም ደግሞ የዘላለምን ሕይወት በተመለከተ መሐመድ በእርግጥ ምን ተናግሯል በእርግጥ የሚያሳምንና ተጨባጭ የሆነ እውነታን ከመሐመድ ትምህርት ውስጥ ማግኘት እንችላለንን?

የዚህ ድረ ገፅ አዘጋጆች የምናምነው እውነትን ፈላጊ የሆኑ ብዙ ሙስሊሞች እንዳሉ እና እነዚህንም ጽሑፎች እንደሚከታተሉ ነው፡፡ በመሆኑም ለእናንተ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር ውስጥ በመሆን የምናቀርብላችሁ ጥሪ ዛሬ ነገ ሳትሉ መጽሐፍ ቅዱስን በማግኘት በማስተዋል እንድታነቡና መልእክቱን እንድትረዱ ነው፡፡ ከዚያም ወጥ በሆነው መልእክቱ መሠረት ኃጢአተኞች መሆናችሁን በመገንዘብ ጌታ እግዚአብሔር በጌታ በኢየሱስ በኩል ያዘጋጀውን መፍትሄ እንድታዩና በዚህም መረዳት ወደ ሕያው እግዚአብሔር ፊት በፀሎት በመቅረብ ንስሐ እንድትገቡና ምህረትንና ይቅርታን ከእርሱ ዘንድ በእምነት እንድትቀበሉ ነው፡፡ ጌታ በፀጋውና በማዳኑ ኃይል ይርዳችሁ አሜን፡፡

የትርጉም ምንጭ: THE DEUTERONOMY DEDUCTIONS: Two Short, Sound, Simple Proofs that Muhammad Was a False Prophet, By David Wood

ለእስልምና መልስ አማርኛ  ዋናው ገጽ